Sunday, September 22, 2024
spot_img

አሜሪካ የኢኮኖሚን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ ማዕቀብ በኢትዮጵያ ላይ ለመጣል እያጤነች መሆኑን አሳወቀች

 

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥቅምት 3 2014 ― አሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተባባሰ ላለው ቀውስ ምላሽ ለመስጠት የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣልን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ አማራጮች እያጤነች እንደምትገኝ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባዩዋ ኔድ ፕራይስ ገልጸዋል፡፡

ኔድ ፕራይስ ይህን የገለጹት የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ ከወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበርና የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ፣ የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሬል፣ የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ጸሐፊ፣ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የፈረንሳይ የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ ጋር በኢትዮጵያ ጉዳይ መምከራቸውን ባሳወቁበት ወቅት ነው፡፡

በውይይቱ ላይ የነበሩ ባለስልጣናት የትግራይ ግጭት ተሳታፊዎች በአፋጣኝ ሁሉን አካታች ወደ ሆነ ውይይት አምርተው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዲያሰፍኑ እና የሃገሪቱን ደህንነት እንዲጠብቁ ጥሪ ማስተላለፋቸው ነው የተነገረው፡፡

በተጨማሪም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ዓለም አቀፍ ሕግን አክብረው የሰብዓዊ እርዳታ ያለ ምንም ገደብ ችግር ለጠናባቸው ኢትዮጵያዊያን እንዲደርስ ይፍቀዱ ማለታቸውንም ኔድ ፕራይስ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የአሜሪካ፣ የአውሮፓ እና የአፍሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት ካካሄዱት ስብሰባ በፊት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን ከአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ተወካይ ኦሌሴጉን ኦባሳንጆ ጋር በኢትዮጵያ ጉዳይ መወያየታቸው ተሰምቷል።

የዛሬ ዓመት ገደማ የሰሜን እዝ መጠቃቱን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት በርካቶችን እየማገደ ቀጥሏል፡፡

ከጦርነቱ ጋር በተገናኘ አሁን የኢኮኖሚን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ ማዕቀብ በኢትዮጵያ ላይ ለመጣል እያጤንኩ ነው ያለችው አሜሪካ፣ በፕሬዝዳንትዋ ጆ ባይደን በኩል ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ለሰላምና መረጋጋት እንቅፋት የሚሆኑ፣ የሰብአዊ አቅርቦትን ወይም የተኩስ አቁም እንዳይደረግ በሚያደናቅፉ፣ እንዲሁም ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በሚፈጽሙ ግለሰቦችና አካላት ላይ ማእቀብ ለመጣል የሚያስችል ትእዛዝ ማስተላለፏ ይታወሳል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በወቅቱ ማእቀብ ለመጣል የሚያስችል ትእዛዝ መፈረማቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ አሜሪካ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ እያራመደችውን አቋም በማንሳት ቅሬታቸውን ገልጸው ነበር፡፡

አሜሪካ በዚያኑ ጊዜ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ተሳታፊ የሆኑ አካላት አስቸኳይ እርምጃ የሚወስዱ ከሆነ ማእቀቡን ለማዘግየት ዝግጁ መሆኗን የገለጸች ቢሆንም፣ ጦርነቱ ከሰሞኑ ተባብሶ መቀጠሉን የሚያመለክቱ መረጃዎች በተለይ በሕወሃት በኩል በስፋት እየወጡ ይገኛሉ፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img