Sunday, November 24, 2024
spot_img

የመንግሥታቱ ድርጅት ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ አስተያየት የሰጡትን የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ኃላፊ ጠራ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 2 2014 ― የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) የኢትዮጵያ ኃላፊ የሆኑት ማውሪን አቺየንግ በመንግስታቱ ድርጅት የተጠሩት ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ‹‹ያልተፈቀደ ቃለ መጠይቆችን›› አድርገዋል በሚል ነው፡፡

በመንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ አስተዳደራዊ እረፍት እንዲወስዱ መደረጋቸው የተሰማው ኃላፊዋ፣ ‹‹ያልተፈቀደ›› በተባለው ቃለ መጠይቅ ለትግራይ ኃይሎች ርህራሄ አላቸው ባሏቸው የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች ወደ ጎን ገሸሽ መደረጋቸውን ተናግረዋል ሲል አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል፡፡

ባለፈው ሳምንት ማውሪን አቺየንግና እና ሌላ ከፍተኛ የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኛ የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል የሚያደርገውን ሕግ ማስከበር ሲል የሚጠራውን ዘመቻ በመደገፍ በርካታ መጣጥፎችን ለሚፅፈው ጄፍ ፒርስ ረዘም ያለ ቃለ መጠይቅ መስጠታቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

በቃለ መጠይቁ ላይ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ኃላፊ ማውሪን ጦርነቱ ከተነሳ በኋላ አዲስ አበባ የገቡ የተባበሩት መንግሥታት የሥራ ባልደረቦቻቸውን በከፍተኛ ሁኔታ በመተቸት መሬት ላይ ያሉ የድርጅቱ ተወካዮችን አግልለዋል ብለዋል። ህወሓትንም ‹‹ቆሻሻ›› እና ‹‹ጨካኝ›› በማለትም ሲሳደቡ እንደሚሰማም ነው የተገለጸው።

በአንድ ወቅትም ህወሓት ከሳዑዲ አረቢያ የተባረሩ የትግራይ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ እንዲላኩ አሲረዋል በማለትም ሲከሱ ይደመጣል የተባለ ሲሆን፣ በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ የነበሩና መውጪያ አጥተው የነበሩ የትግራይ ተወላጅ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ እንዲላኩ ጥያቄ እንደቀረበላቸውና ሩዋንዳም እንዲላኩ የተፈለገው ለሌላ አላማ እንደሆነ ሲናገሩም ይሰማል።

ባለፈው ሳምንት ኤኤፍፒ ተመልክቼዋለሁ ባለው የውስጥ ማስታወሻ፣ ኃላፊዋ በበኩላቸው ‹‹በጥልቅ ተረብሻለሁ እናም አዝኛለሁ›› ካሉ በኋላ፣ ቃለ ምልልሱን ‹‹በስውር እንደተቀዳና ተመርጦ አርትኦት እንደተደረገበት›› ተናግረዋል ነው የተባለው።

ሰኞ እለት የአይኦኤም ዋና ዳይሬክተር አንቶኒዮ ቪቶሪኖ የኃላፊዋን አስተያየቶች አስመልክቶ ደብዳቤ መጻፋቸው በዘገባው የተጠቀሰ ሲሆን፣ ‹‹በድምፁ ላይ በድርጅቱ አባል የተሰጡት አስተያየቶች ከአይኦኤም መርሆች እና እሴቶች ጋር አይዛመዱም፣ በምንም መልኩ የድርጅቱ አቋም እንደተገለጸ ተደርጎ መታየት የለበትም›› ብለዋል።

ደብዳቤው ማውሪን አቺየንግን በስም የማይጠቅስ ቢሆንም ምርመራው እስኪካሄድ ድረስ ወዲያውኑ እንደተጠሩ እና የአስተዳደር እረፍት ያደርጋሉ ተብሏል።

ጉዳዩን አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ አቀባይ ቢልለኔ ሥዩም በትዊተር አስተያየታቸውን አስፍረዋል፡፡ ቢልለኔ በአስተያየታቸው ‹‹የተባበሩት መንግሥታት ሥርዓት ከሽብርተኛው ቡድን ህወሓት ጋር ባለው ግንኙነት ተቋማዊ አድሏዊነትን መከተሉን በግልፅ በመናገራቸው ማውሪን አቺየንግ ላይ የተጣለው አስተደዳራዊ እረፍት በጣም የሚረብሽ ነው›› ብለዋል።

አክለውም ‹‹በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ በከፍተኛ የሥልጣን እርከኖች ያለው ውስጣዊ እና የውጭ ተፅእኖ ፓለቲካ በጥልቀት መመርመር እንዳለበት›› ገልጸዋል፡፡

የኃላፊዋን ከሥራ ኃላፊነታቸው መነሳት በያዝነው ሳምንት ሰኞ በተፃፈና የፈረንሳዩ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ተመልክቼዋለሁ ባለው ደብዳቤ አረጋግጫለሁ ያለ ሲሆን፣ በበለጠ የእርዳታ ሥራውን እንደሚያዳክመውም ጠቅሷል።

በቅርቡ መንግስት በውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ገብተዋል ያላቸውን ከፍተኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ማባረሩና ጉዳዩም ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img