Sunday, October 6, 2024
spot_img

በአስፈፃሚ አካላት መልሶ ማደራጀት የፈረሱ ከ30 በላይ የፌደራል መስሪያ ቤቶች ሠራተኞች እጣ ፋንታ አልታወቀም ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ መስከረም 29፣ 2014 ― ባለፈው ሰኞ መስከረም 24፣ 2014 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀውን የአስፈፃሚ አካላትን መልሶ ስለማደራጀት የሚደነግግ አዋጅ ተከትሎ 32 ያህል የፌደራል መስሪያ ቤቶች ስለመታጠፋቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡

የታጠፉት መስሪያ ቤቶች ቀደም ሲል በአዋጅ ተሰጥቷቸው የነበረው መብትና ግዴታቸው ወደ አዲሶቹ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች እንደሚተላለፍ አዋጁ አመልክቷል፡፡

በዚሁ አዋጅ የታጠፉና እርስ በእርስ የተዋሃዱት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ ሰራተኞች ዕጣ ፋንታ ምን እንደሚሆን በምክር ቤቱ ማብራሪያ አልተሰጠበትም፡፡ ነገር ግን ለመታጠፋቸው ከበጀትና ከሐብት አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ምክንያት ቀርቧል፡፡

አዲስ በጸደቀው አዋጅ መሠረት የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣንና የምርት ገበያ ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች ፈርሰው፣ ወደ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ስር የነበረው ቱሪዝም ኢትዮጵያ ፈርሶ መብትና ግዴታዎቹ ለቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና አቶ ንጉሡ ጥላሁን ይመሯቸው የነበሩት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ ከፌደራል ከተሞች ስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ጋር ጨምሮ ፈርሰው መብትና ግዴታዎቻቸው አዲስ ወደ በተቋቋመውና የቀድሞዋ የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ተሹመውበት ለአዲሱ የስራና ክህሎት ፈጠራ ሚኒስቴር ተላልፏል፡፡

በሌላ የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ፈርሶ መብቱና ግዴታዎቹ አዲስ ለተቋቋመውና በወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ለሚመራው የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተባባሪያ ኤጀንሲ፣ የፌደራል ከተሞች መሬትና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የፈረሱ ሲሆን፣ መብትና ግዴታዎቻቸው አዲስ ለተቋቋመው የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የውሃ ልማት ኮሚሽን፣ የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣንና የውሃ ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤትም በተመሳሳይ ፈርሰው፣ መብትና ግዴታዎቻቸው ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ዶክተር ሳሙኤል ኡርካቶ ሲመሩት የነበረው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ስትራቴጂ ማዕከል ፈርሰው መብትና ግዴታቸው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በተሾሙበት የትምህርት ሚኒስቴር ተጠቃሏል፡፡

ለዓመታት የዘለቀው ሀገር አቀፍ የኤችአይቪ/ኤድስ መከላካያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት በጤና ሚኒስቴር ሲጠቃለል፣ በአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ስም የተሰየመው የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ፈርሶ መብትና ግዴታዎቹ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ለሚመሩት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተሰጥቷል፡፡

የእንስሳት መድሃኒትና መኖ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አዲስ ለተቋቋመው የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን፣ ብሔራዊ የቆላ ዝንብና የገንዲ በሽታ መቆጣጠሪያና ማጥፊያ ኢንስትቲዩት ለእንስሳት ጤና ኢንስትቲዩት፣ ብሔራዊ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ኢንስትቲዩቲ እና የኢትዮጵያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት አዲስ ለተቋቋመው የእንስሳት ልማት ኢንስትቲዩት፣ የኢትዮጵያ አፈር ሀብት ኢንስትቲዩትና የኢትዮጵያ ግብርና ሴክቴሪያት በአዋጅ ለተቋቋመው አዲስ መስሪያ ቤት ለግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት፣ የፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ልማት ኤጀንሲ ለኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ባለስልጣን፣ የምግብና የመጠጥ ፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪዎች ልማት ኢንስትቲዩት፤ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩትና የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት እንዲሁም የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስትቲዩት ፈርሰው መብትና ግዴታዎቻቸው በአዋጁ ለተቋቋመው የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት ተላልፏል፡፡

የነዳጅና ነዳጅ አቅርቦት ስርጭት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን እና የኢነርጂ ባለስልጣን ፈርሰው ወደ ነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን፣ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩትና የኬሚካል ኮንስትራክሽን ግብኣት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት የፈረሱ ሲሆን መብትና ግዴታዎቻቸው አዲስ ወደ ተቋቋመው የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት ተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እና ጂኦፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስትቲዩት ፈርሰው ስፔስ ቴክኖሎጂ እና ጂኦፓሻል ኢንስትቲዩትን ፈጥረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጨረራ መከላከያ ባለስልጣን የፈረሰ ሲሆን መብትና ግዴታዎቹ አዲስ ለተቋቋመው የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ማሰልጠኛ ኢንስትቲዩት እና የስትራቴጂክ ጉዳዮች ኢንስትቲዩት ፈርሰው መብትና ግዴታዎቻቸው በአዋጁ ለተቋቋመው የውጭ ግንኙነት ኢንስትቲዩት ተላልፈዋል፡፡

የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ እና የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስትቲዩት ፈርሰው መብትና ግዴታዎቻቸው ለቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስትቲዩት ከተሰጡት መስሪያ ቤቶች መካከል ይገኛሉ፡፡

የቀድሞዎቹን መስሪያ ቤት ይመሩ የነበሩ ሚኒስሮች አዲስ ለተሾሙት የሥራ ርክክብ ማድረጋቸው እየተነገረ የሚገኝ ሲሆን፣ ከታጠፉት መካከል የሆነውና ሚኒስትሩ ከአዲሱ መንገስት ምስረታ አንድ ሳምንት ቀድሞ መልቀቃቸውን ያስታወቁት የሕጻናት፣ ሴቶች እና ወጣቶች ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፊልሳን ዐብዱላሂ ሥልጣናቸውን ለዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አስረክበዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img