Sunday, September 22, 2024
spot_img

የመንግሥታቱ ድርጅት በመከራ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ከመርዳት ውጪ ፖለቲካዊ አጀንዳ የለውም ሲሉ አንቶንዮ ጉቴሬዝ ገለጹ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ መስከረም 28፣ 2014 ― የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (የተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ ድርጅታቸው በመከራ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ከመርዳት ውጭ ሌላ ፖለቲካዊ አላማ የለውም ሲሉ ጽፈዋል፡፡

ይህን በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት ዋና ጸሐፊው፣ በትግራይ በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለማስቆም የትኛውንም ነገር በማድረግ በማስቆም፣ በሁሉም ቦታዎች ላይ የሰብአዊ አቅርቦትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

አንቶንዮ ጉቴሬዝ በዋና ጸሐፊነት የሚመሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በጸጥታው ምክር ቤት በኩል ረቡዕ መስከረም 26፣ 2014 ለአስረኛ ጊዜ የተሰበሰበ ሲሆን፣ እርሳቸውም በዚሁ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት መስከረም 20፣ 2014 አገር ለቃችው ውጡ በማለቱ ‹‹አስደንግጦኛል›› ያሉበትን የተመድ ሠራተኞችን በተመለከተ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

በዚሁ ስብሰባ ላይ ጉቴሬዝ በተመድ የኢትዮጵያ ልዑክ የሆኑት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ መንግስት ሠራተኞቹን ከማባረሩ በፊት ለድርጅቱ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መላኩን መጥቀሳቸውን ተከትሎ ማስረጃ ይቅረብልኝ ሲሉ ሙግት ገጥመው ነበር፡፡  

ዋና ጸሐፊው በዚሁ ስብሰባ እና ቀደም ባሉት መግለጫዎቻቸው መንግስት ከሰሞኑ ያሳለፈውን ውሳኔ አስመልክቶ ሠራተኞቹ ባላቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥበቃ ተቀባይነት እንደሌለው እና ግዛቲቷን ለቀው እንዲወጡ መጠየቁ በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር መሠረት ከአንድ አገር ግዴታ ጋር የማይጣጣም ነው ሲሉም ነበር፡፡

በምክር ቤቱ ስብሰባ የመንግሥታቱ ድርጅት በኢትዮጵያ ያለው አንድ አጀንዳ ብቻ ነው ያሉት ዋና ጸሐፊው፣ ይህ አጀንዳም ‹‹የትግራይ፣ የአማራ፣ የአፋር፣ እና የሶማሊ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ናቸው›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝቦች እየተሰቃዩ ነው። ይህን ሰቆቃ ከማስቀም ውጪ ሌላ አላማ የለንም›› ሲሉም አክለው ነበር፡፡ ጉቴሬዝ ይህንኑ ተመሳሳይ አቋም በዛሬ እለት በትዊተር ደግመውታል፡፡

ለተመድ ሠራተኞች መባረር በመንግስት ከቀረቡት ምክንያቶች መካከል ለትግራይ ሕዝብ የመጣ እርዳታ ለሕወሓት መስጠት፣ በፀጥታ ጉዳይ የተደረጉ ስምምነቶች መጣስ፣ የግንኙነት መሳሪያዎችን ለሕወሀት ማቀበል፣ የእርዳታ እህል ጭነው ትግራይ የገቡና ሕወሀት ለወታደራዊ እንቅስቃሴ የሚጠቀምባቸውን 400 የሚደርሱ ተሽከርካሪዎችን ለመመለስ ተደጋጋሚ እንቅፋት መፍጠር እንዲሁም የተሳሳተ መረጃ ማሰራጨት የሚል መጠቀሱ መነገሩ ይታወሳል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img