Monday, September 23, 2024
spot_img

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እስከ ፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መሻሻል ካላሳየ ማእቀብ እንዲጣል የአውሮፓ ፓርላማ ጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ መስከረም 28፣ 2014 ―

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እስከ ፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መሻሻል ካላሳየ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ላይ ማእቀብ እንዲጣል የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ጠይቀዋል፡፡

 

ፓርላማው ትላንት ሐሙስ መስከረም 27፣ 2014 ያደረገውን ስብሰባ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ላይ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲበጅለት ጠይቀው፣ ነገር ግን በጦርነቱ አካባቢ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ እስከ ፈረንጆቹ ጥቅምት ወር መጨረሻ ማለትም ጥቅምት 21፣ 2014 ድረስ በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻል የማያሳይ ከሆነ ኮሚሽኑ በጦርነቱ ተሳታፊዎች ላይ ማዕቀብ እንዲጥል ጠይቀዋል።

ፓርላማው ዕቀባው ይመለከታቸዋል ያላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኤርትራ መንግሥት እና ሕወሓትን ጨምሮ ግጭቱ እንዲራዘም እና እንዲባባስ አስተዋጽኦ አላቸው ያላቸውን አካላት ነው፡፡

የአውሮፓ ፓርላማ ትላንት ባደረገው ስብሰባ ላይ የቀረበው ይኸው የውሳኔ ሐሳብ በ618 ድጋፍ፣ በ4 ተቃውሞ እና በ58 ድምጸ ታቅቦ ተቀባይነት ማግኘቱን ነው ያመለከተው፡፡

በሌላ በኩል ፓርላማው በትግራይ እንደ ምግብ፣ መድኃኒት እና ነዳጅ ያሉ መሠረታዊ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች ላይ ይፋዊ ያልሆነ እገዳ እንዲቆም ለየሚመለከታቸው ብሔራዊ እና አህጉራዊ አካላት ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ በአጎራባቾቹ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ድጋፍ እንዲደረግ አሳስቧል።

ፓርላማው በውሳኔ ሃሳቡ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ ሆነ ብለው ንሑሃን ዜጎችን ዒላማ ማድረጋቸውን አጥብቆ ሲያወግዝ፣ የሕወሓት ኃይሎችን ጨምሮ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ሕፃናትን ለጦርነት መመልመላቸው እንዲሁም የቀጠለው አስገድዶ መድፈር እና ጾታዊ ጥቃቶችን ተቃውሟል።

ፓርላማው አጎራባች አገራት ግጭቱን ሊያባብሱ ከሚችሉ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ራሳቸውን እንዲቆጥቡም ጠይቋል።

የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ጨምረውም የኢትዮጵያ መንግሥት በሺዎች የሚቆጠሩ በትግራይ ክልል ከሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች የተፈናቀሉ ኤርትራውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጥበቃ እና ድጋፍ እንዲያደርግ የሕብረቱ ፓርላማ አባላት ጠይቀዋል።

በተጨማሪም የደረሱበት ያልታወቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ዕጣ ፈንታ ምን እንደሆነ መንግሥት እንዲያሳውቅ የፓርላማ አባላቱ ጠይቀዋል።

አስራ አንድ ወራት ባስቆጠረው ትግራይ ውስጥ ተጀምሮ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ጦርነት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሰብአዊ እርዳታ እንዲጠብቁ ሲያስገድድ፣ መቶ ሺዎችን ደግሞ በረሃብ ሁኔታ ውስጥ መጣሉን የተባባሩት መንግሥታት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img