Sunday, October 6, 2024
spot_img

የተመድ ዋና ጸሐፊ ከኢትዮጵያ በተባረሩት የድርጅታቸው ሠራተኞች ላይ የተጻፈ ማስረጃ ካለ እንዲቀርብ ጠየቁ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ መስከረም 27፣ 2014 ― የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (የተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ ባለፈው ሳምንት መንግስት ያባረራቸው ሰባት ሠራተኞችን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ለተመድ ድርጅቶች በጽሑፍ የቀረበ ሰነድ ካለ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡

ጉቴሬዝ ይህንኑ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት የትግራይ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ትላንት ለአስረኛ ጊዜ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን ለሚወክሉት ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ነው፡፡ ዋና ጸሐፊው ይህንኑ ጥያቄ ከዚህ ቀደም ለሁለት ጊዜያት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቅርበው ምላሽ እንዳላገኙ ገልጸዋል፡፡ ይህ መደረጉ በድርጅቴ ውስጥ ምን እየተደረገ እንደሆነ ለማወቅ ይረዳኛል ሲሉም ጉቴሬዝ ተደምጠዋል፡፡

አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በበኩላቸው በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አገራት የነበሩ የተመድ ሠራተኞች እንደተባረሩ አስታውሰው፣ ሆኖም አንድም ጊዜ ቢሆን ጉዳዩ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ቀርቦ ያውቃል ወይ ሲሉ ሌላ ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡

ከጉቴሬዝ በቀረበው የሰነድ ካለ ይቅረብልኝ ጥያቄ ጋር በተገናኘ ብዙ ማብራሪያ ያልሰጡት አምባሳደሩ፣ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ምንም ዐይነት የተጻፈ መረጃ ሲኖር ወደ ቢሮዎ እንልካለን ሲሉ አጠር ያለ ምላሽ ሰጥተው አልፈውታል፡፡

መንግስት ሰባቱን የተመድ ሠራተኞች በአስቸኳይ የኢትዮጵያን ግዛት ለቃችሁ ውጡ ያላቸው ባለፈው ሳምንት መስከረም 20፣ 2014 ነበር፡፡ ሠራተኛ ከተባረሩባቸው የተመድ ቢሮዎች አንዱ የሆነው የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የኮሚኒኬሽን ባለሞያ ሐያት አቡ ሳሊህ ከሁለት ቀናት በፊት ለመገናኛ ብዙኃን ሠራተኞቹ የኢትዮጵያን ግዛት ለቀው መውጣታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ሆኖም ሠራተኞቹ መቼ እና እንዴት እንደወጡ የተገለጸ ነገር የለም፡፡

ይህንኑ ተከትሎ በጉዳዩ ላይ ጠንከር ያለ ምላሽ ስትሰጥ የቆየችው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ሰባቱን ሠራተኞች እንዲመለሱ በማድረግ ‹‹የነፍስ አድን ሥራቸውን እንዲቀጥሉ›› ጠይቀዋል፡፡

በትላንትናው የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባም አገሪቱን በመንግስታቱ ድርጅት የሚወክሉት አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንስፊልድ ተመሳሳይ አቋም አንጸባርቀዋል፡፡   

የኢትዮጵያ መንግስትን ውሳኔ ‹‹በቂ ምክንያት ያልቀረበበት›› ነው ያሉት ሊንዳ፣ አካሄዱንም ቢሆን ‹‹ትክክለኛውን መንገድ ያልተከተለ ነው›› ሲሉ ተችተውታል፡፡ አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔውን እንዲቀለብስ የጠየቁ ሲሆን፣ ይህ ካልተፈጸመ የጸጥታው ምክር ቤት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

አሜሪካው ሠራተኞቹን ኢትዮጵያ መመለስ አለባት የሚል አቋም ብታንጸባርቅም፣ የፀጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያ ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ግን ከሰሞኑ የመንግስታቱ ድርጅት በተባረሩት ሠራተኞች ምትክ ሌሎችን እንዲልክ መጠየቃቸው መነገሩ አይዘነጋም፡፡

ትላንት በተካሄደው የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ቻይና እንደ ቀደሙት ጊዜያት ሁሉ የኢትዮጵያን አንድነትእንዲጠበቅ ድጋፏን አንጸባርቃለች፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምር ቤት መንግስት የመንግስታቱ ድርጅት ሠራተኞችን ካባረረ በኋላ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ሲመክር ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img