Sunday, October 6, 2024
spot_img

በጠ/ሚ ዐቢይ ካቢኔ ያልተካተቱት ዶክተር ስለሺ በቀለ ለሌላ አገራዊ ኃላፊነት ሥምሪት መዘጋጀታቸውን ጠቆሙ

በዛሬው እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔያቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ሲያስጸድቁ ያልተካከተቱት የቀድሞው የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ ለሌላ አገራዊ ኃላፊነት ሥምሪት መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

በዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔ ቀድሞ ዶክተር ስለሺ በቀለ የሚመሩት የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአዲስ አደረጃጀት ተከፍሎ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ሚኒስትር ተደርገው ሲሾሙ፣ ዶክተር ሐብታሙ ኢተፋ ደግሞ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ተደርገዋል።

ላለፉት 5 አመታት የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትርን የመሩት ዶክተር ስለሺ፣ ለአዲሶቹ ተሿሚዎች መልካም ምኞታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ የእርሳቸውን ጉዳይ በተመለከተ ግን “በቀጣይ አገሬ በምትፈልገኝ አገልግሎት የምሰማራ ይሆናል” ብለዋል።

በቀድሞ መስሪያ ቤታቸው ኃላፊነት ወቅት “ብዙ አስቸጋሪ ጊዜያትንም አሳልፈናል” ያሉት ዶክተር ስለሺ በቀለ፣ “ግድባችንም በጥቂት ወራት ሀይል ያመነጫል፡፡ በዚህና በሌሎችም መስኮች ያደረግሁት አስተዋጽኦ በፈታኞቹ ወቅቶችና ሰአታት አገሬን ቀና አድርጓታል ብዬ አምናለሁ” ሲሉም አስፍረዋል።

ዛሬ ይፋ በተደረገው የጠቅላይ ኢኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔ ውስጥ የቀድሞውን ሚኒስትር በቦታቸው አለመመደባቸውን ተከትሎ ይህ ለምን እንደተደረገ የሚጠይቁ ድምጾች በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ሲስተጋቡ ተስተውሏል።

ተሰናባቹ ሚኒስትር በተለይ ከሱዳንና ግብጽ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና ኦፕሬሽን በተመለከተ ከሚካሄደው ከባድ እና የተራዘመ ድርድር ውስጥ ኢትዮጵያን ወክለው ከፊት ቀርበው በፈጸሙት ተጋድሶ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ አክብሮት የሚቸራቸው ናቸው።

የሕዳሴው ግድብ ድርድር ከስምምነት ሳይደረስ የግድቡ ውሃ ሙሌት መከናወን የለበትም በሚል ሱዳንና ግብጽ ለዓመታት አጥብቀው ቢከራከሩም ‘ስምምነት ተደረሰም አልተደረሰ ኢትዮጵያ ግድቡን በውሃ መሙላቷን አታቆምም’ በማለት የአገራቸውን ቁርጥ ያለ አቋም በተደጋጋሚ ግልጽ አድርገው ኢትዮጵያ የሁለተኛውን ዙር የግድቡን ውሃ ሙሌት አከናውናለች።

ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆኑት ዶክተር ኢንጂኒየር ስለሺ በቀለ በአሜሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥራቸውን ለቀው አገራቸውን ለማገልገል የመጡት በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በቀረበላቸው ጥሪ ነበር።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img