Sunday, September 22, 2024
spot_img

ፌስቡክ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአገራት ላይ ፈጽሞታል በተባለ ድርጊት በቀድሞ ሠራተኛው ውንጀላ ቀረበበት

ከትላንት በስትያ መስከረም 24 ምሽት ለስድስት ሠዐታት ከአገልግሎት ውጭ ሆኖ መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው ግዙፉ የፌስቡክ ኩባንያ፣ ከቀድሞ ሠራተኛው ኢትዮጵያን ጨምሮ በአንዳንድ ሀገራት የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን መግታት እየቻለ አላስቆመም የሚል ውንጀላ ቀርቦበታል፡፡

ለሁለት ዓመታት ያህል በኩባንያው የሠሩት የዳታ ሳይንቲስቷ ፍራንሴስ ሃውገን ይህንኑ በአሜሪካ ሕግ አውጭ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ተናግረዋል።

እንደ ቀድሞዋ የኩባንያው ባልደረባ ከሆነ ፌስቡክ በተለይ ከእንግሊዝኛ ውጭ ባሉ ቋንቋዎች የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን በአግባቡ አልተቆጣጠረም፡፡ እኚሁ ግለሰብ በኩባንያው ላይ ላነሱት ውንጀላ በአስረጂነት ደጋግመው የኢትዮጵያን ስም አንስተዋል፡፡

ኩባንያው የጥላቻ ንግግርን ከመቆጣጠር ይልቅ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ለሚስገባው ትርፍ እንደሆነም ሠራተኛዋ አክለው ገልጸዋል። የዳታ ሳይንቲስቷ ፌስቡክ ይህን አካሄድ በመምረጡ የበዛ መከፋፈል፣ በርካታ ውሸት እና ስጋት ማስከተሉን በመግለጽ፣ በኦንላይን ሚዲያው የሚሠራጩ አደገኛ ንግግሮች በሰዎች ላይ እስከ ግድያ ማስከተላቸውንም አመልክተዋል፡፡

በአሜሪካ ሕግ አውጭ ኮሚቴ ፊት ቀርበው የፌስቡክን ገመና ያጋለጡት የዳታ ሳይንቲስቷ ፍራንሴስ ሃውገን፣ ከዚህ ቀደም ኩባንያውን ከመልቀቃቸው ቀድሞ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የኩባንያውን ምስጢራዊ ሰነዶች ቅጂ ለሕግ አውጪዎች እና ለተቆጣጣሪ አካላት በማጋራት መቀመጫውን በአሜሪካ ኒውዮርክ ባደረገው ግዙፉ ዎልስትሪት ጆርናል ጋዜጣ ላይ እንዲታተም አድርገዋል፡፡

በተጨማሪም እርሳቸው በኩባንያው በነበሩበት ወቅት አንድ አሳዛኝ እውነት ተገንዝቤያለሁ ያሉት የቀድሞዋ የኩባንያው ባልደረባ፣ ይህንኑ እውነታ ከፌስቡክ ውጭ ያለ ማንም ሰው እንደማያውቅ ያመለከቱ ሲሆን፣ በርከት ያሉ ጠቃሚ ያሏቸው መረጃዎች ከዓለም መንግስታት እንደሚደበቅ ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው በቀድሞ ባልደረባው የቀረበበትን ውንጀላ በተመለከተ መስራቹ ማርክ ዙከርበርግ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ መስራቹ በምላሻቸው የተከወኑ ሥራዎች ከአውድ ውጭ ትርጓሜ ተሰጥቷቸው ለሚፈጠር ሐሰተኛ ትርክት ቁብ እንደማይሰጡ ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም ኩባንያቸው በተለይ የሚያተኩረው የፌስቡክ ምርቶች በሕጻናት ያለው ተጽእኖ ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የፌስቡክ መስራችና ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ ከትላንት በስትያ ኩባንያቸው ለሰዓታት አገልግሎት በማቋረጡ 7 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገንዘብ ማጣታቸው ተነግሯል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img