Sunday, November 24, 2024
spot_img

ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ቢጠሩም የቀሩ ዲፕሎማቶች መኖራቸውን መንግሥት አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ መስከረም 23፣ 2014 ― ኢትዮጵያን በውጭ አገሮች የወከሉ ዲፕሎማቶች ለመጀመርያ ዙር ዓመታዊ ስብሰባና አቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ከተጠሩት ውስጥ አብዛኛዎቹ ቢመለሱም፣ የተወሰኑት በዚያው መቅረታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንታዊ መግለጫቸው እንዳስታወቁት፣ ተጠርተው የቀሩትን ዲፕሎማቶች ቁጥር ባይናገሩም፣ ከተጠሩት አብዛኛዎቹ መምጣታቸውንና ያልመጡም እንዳሉ ጠቁመው፣ ጥሪ ያልተደረገላቸው በቀጣይ እንደሚጠሩ ተናግረዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲፐሎማቶችን ወደ አገር ቤት ሲጠራ ጥሪውን ባለመቀበል ወደ አገር ቤት ያልተመለሱ ስለመኖራቸው መረጃ አግኝቻለሁ ያለው ሪፖርተር ጋዜጣ፣ የግለሰቦችን ማንነት በዝርዝር ለማረጋገጥ እንዳልተቻለ ዘግቧል።

‹‹ያለሁበት አገር ካልቀረሁ ብሎ የፈለገ አካል መጥፋት መብቱ ነው፤›› ያሉት ቃል አቀባዩ፣ መጥፋት የፈለገ ዲፕሎማት ቢኖርም ለማንም አይጠቅምም ብለዋል፡፡

በሌሎች አገሮች በተለይም በምዕራባውያኑ ዘንድ አንድ ዲፕሎማት የመንግሥትን ፖሊሲ አልቀበልም ካለ በቃኝ ማለት እንደሚችል የጠቆሙት ዲና፣ ‹‹ኢትዮጵያን የሚወክል ዲፕሎማት ተመለስ ሲባል አልመለስም›› ካለ በጦር ግንባር አገርን ለመጠበቅ ከሚዋደቀው ሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር በአስተሳሰብ አይገናኝም ብለዋል፡፡

‹‹አብዛኞቹ ዲፕሎማት ይህ የገባቸው ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን የሚሳሳት ካለ  ይቅናው ብሎ መተው ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሁን እያካሄደ ያለው የሁለት ዙር የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ሲጠናቀቅ፣ ዲፕሎማቶችን እንደገና የመመደብ ሥራ እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡

ዲፕሎማቶች እንደ አቅማቸውና ዝግጅታቸው ታይቶ እንደገና እንዲመደቡ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታውቀዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img