በታዳጊ ሀገራት ላይ ከአንድ ወገን የሚጣልን የማዕቀብ እርምጃ እንቃወማለን ሲሉ ቻይና እና ሌሎች 29 የዓለም ሀገራት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደብዳቤ አስብተዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቻይና ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ዣን ጁን ደብዳቤውን በተወካይነት ያስገቡ ሲሆን፣ በደብዳቤው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ኢኮኖሚ ላይ የፈጠረውን ከባድ ተጽዕኖ በመገንዘብ ሁሉም የተመድ አባል ሀገራት በዓለም አቀፍ ትብብር ላይ የተመሠረተ ዓለም አቀፋዊ ምላሽ በመስጠት ለወረርሽኙ ተፅዕኖ መፍትሄ ለመስጠት እንዲሰሩ ሀገራቱ ጠይቀዋል።
የዓለም አቀፍ ግንኙነቶች መሠረታዊ መርሆዎችንና የተመድ ቻርተር እና ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በሚፃረር መልኩ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ላይ የሚወሰዱ ማናቸውም የአንድ ወገን አስገዳጅ እርምጃዎች ያሳስበናል ሲሉ ሀገራቱ በደብዳቤው ገልፀዋል።
በመሆኑም እገዳው የታሰበባቸው ሀገራት ላይ የሚደረጉት እርምጃዎች ሙሉ በሙሉ እና በፍጥነት እንዲነሱ በመጠየቅ ጉዳት የደረሰባቸው ሀገራት በቂ ሀብቶችና ለወረርሽኙ ምላሽ እና ማገገሚያ ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
አያይዘውም መንግስታት በዓለም አቀፍ ሕግ እና በተባበሩት መንግስታት ቻርተር መሠረት ወደፊትም የአንድ ወገን ማዕቀቦችን ከመጫን እንዲቆጠቡ በደብዳቤው አፅንኦት ሰጥተዋል።
የተቃውሞ ደብዳቤውን ለተመድ የላኩት አባላት፦ አንጎላ፣ ቤላሩስ፣ ቦሊቪያ፣ ቬኔዙዌላ፣ ቡሩንዲ፣ ካምቦዲያ፣ ካሜሩን፣ ቻይና፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኩባ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ዶሚኒካ፣ ግብፅ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢራን፣ ላኦስ፣ ናሚቢያ፣ ኒካራጓ፣ ፓኪስታን፣ የሩሲያ ፌዴሬሽን፣ ሴይንት ቪንሰንት እና ግሬናዲንስ፣ አንቲጓ እና ባርቡዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ስሪላንካ፣ ፍልስጤም፣ ዙምባቡዌ እና ሶሪያ ናቸው።