Saturday, October 5, 2024
spot_img

በአልማክቱም ፋውንዴሽን ላይ ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ በማስጠንቀቂያ ተነሳ

 

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ መስከረም 22፣ 2014 ― የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ በአልማክቱም ፋውንዴሽን ላይ ጥሎት የነበረውን እገዳ በመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ ማንሳቱን አስታውቋል፡፡ ኤጀንሲው እገዳውን ያነሳው ድርጅቱ የፈጸመውን የህግ ጥሰት አምኖ በመቀበሉ እና ለስህተቱም ይቅርታ በመጠየቁ መሆኑን ገልጿል።

አል-ማክቱም ፋውንዴሽን ለሶስት ወራት እንቅስቃሴ እንዳያደርግ በኤጀንሲው እገዳ የተጣለበት በሐምሌ 2013 ነበር።

አል-ማክቱም ፋውንዴሽንን ለእገዳ ካደረጉት ሁለት ምክንያቶች የመጀመሪያው፤ ‹‹የውጭ ሀገር ዜጎችን ያለስራ ፍቃድ አሰማርቷል›› የሚል ሲሆን፣ ድርጅቱ በዚህ ረገድ የፈጸመው የህግ ጥሰት ላይ ተገቢውን እርምት ያደረገ መሆኑን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ በትላንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ያለ ስራ ፍቃድ ያሰማራቸው የውጭ ሀገር ዜጎች ከሀገር የወጡበትን መረጃ በማቅረቡ እገዳው እንደተነሳለት ኤጀንሲው አስታውቋል። 

ፋውንዴሽኑ ለመታገዱ በሁለተኛነት የተጠቀሰበት ምክንያት ‹‹የሀገሪቱን ህገ መንግስት ባለማክበር እና ለህግ ተገዢ ባለመሆን፤ በማን አለብኝነት እንቅስቃሴ ማድረጉ በመረጋገጡ›› መሆኑን ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም ገልጾ ነበር። ከዚህ ጋር የተያያዘው የህግ ጥሰት፤ ፋውንዴሽኑ በአዲስ አበባ ከገነባቸው ሁለት ትምህርት ቤቶች ጋር በቀጥታ የተገናኘ መሆኑም ተመልክቷል።  

በዱባይ ምክትል ገዢ ሼክ ሀምዳን ቢን ራሺድ አል-ማክቱም የተመሰረተው ፋውንዴሽኑ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ69 ሀገራት ላይ ትምህርት ላይ መሰረት ያደረገ የእርዳታ ስራዎችን ይሰራል። ፋውንዴሽኑ በ22 የአፍሪካ ሀገራት 40 ትምህርት ቤቶችን ያቋቋመ ሲሆን፤ በኢትዮጵያም በአዲስ አበባ የካ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች ትምህርት ቤቶች አስገንብቶ ከሶስት ዓመታት በፊት ስራ አስጀምሯል። 

ከፋውንዴሽኑ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ የሆላንዱ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን እና የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል እገዳ እንደተጣለባቸው ይታወሳል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረ ገጽ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ትዕግሥት ዳኝነትን ጠይቄ ‹‹እስካሁን ማስረጃ አላቀረቡም፣ እኛም እያጣራን ነው›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተውኛል ብሏል፡፡  

ሁለቱ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የታገዱት፤ የሐሰት መረጃዎችን በማህበራዊ ሚዲያዎች እና ሌሎች መገናኛ ዘዴዎች አሰራጭተዋል በሚል ነው። ድርጅቶቹ በተጨማሪም ያለኤጀንሲው ፍቃድ እና እውቅና፤ የውጭ ሀገር ዜጎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት እንዲሁም በማሰራት ሌላ ውንጀላ ቀርቦባቸው ነበር።  

የሆላንዱ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በኤጀንሲው ለመታገዱ ‹‹የሳተላይት ሬዲዮኖችን ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቶ አፍራሽ ለሆነ ተግባር እንዲውሉ አድርጓል›› በሚል በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ተወንጅሎ ነበር። የኤጀንሲውን እገዳ ተከትሎ፤ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ስራውን ማቋረጡን በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ አስታውቋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img