Monday, October 7, 2024
spot_img

አገር ለቀው እንዲወጡ በታዘዙ የውጭ ዜጎች ላይ የተወሰደው እርምጃ ሕጋዊነትን ለማስፈን የተወሰነ መሆኑን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ

በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩና ከተሰማሩበት ዓላማ ውጪ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚጎዳ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ ሰባት የውጭ ዜጋ ሠራተኞች ላይ የተወሰደው እርምጃ ሕጋዊነትን ለማስፈንና ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ሰባት ሠራተኞች በ72 ሰዓታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ የኢትዮጵያ መንግሥት ማዘዙን ተከትሎ ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ግለሰቦቹ ከአገር እንዲወጡ የታዘዙት ከተሰጣቸው ኃላፊነት ውጪ ሲንቀሳቀሱና በሕገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው ነው፤ ይህ ደግሞ ሕጋዊነትን ለማስፈን የተወሰደ እንዲሁም ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ፤ ማንኛውም ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋምም ሆነ ግለሰቦች ሲገቡ ፍቃድ አላቸው፡፡ የሚሰሩትም በፍቃድ ሲሆን፣ የትኛውም ተቋምና ግለሰብ ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጪ ሲንቀሳቀሱ ከተገኙ ተግባሩ ሕገወጥ ነው፡፡ ከአገር እንዲወጡ በታዘዙት ግለሰቦች የሆነውም ይኸው ነው፡፡

«አንዳንዱ ለሕክምና ሥራና ለጤና አገልግሎት ይመጣና፣ ጤናን በሚያዛቡና የኅብረተሰቡን ሰላም በሚያደፈርሱ ተግባራት ላይ ይሰማራል፣ ለውሃ ቁፋሮ ይመጣና አገር ሲቆፍር ይውላል፡፡ ይህ ዓይነት ተግባር ደግሞ በየትኛውም አገር አይፈቀድም፤» ያሉት አምባሳደር ዲና፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌላም አገር የአንድን አገር ሉዓላዊነት፣ የአንድን አገር ደህንነት፣ የአንድን አገር ሰላም የሚያደፈርሱ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ክልክል መሆናቸውን መናገራቸውን የኢዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img