የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (ዩኤንዲፒ) በቅርቡ ያስተዋወቀው አፍሪካውያን ጀማሪ የስራ ፈጣሪዎችን የሚደግፈው መርሃ ግብር 1 ቢሊዮን ዶላር በማሰባሰብ ከ1 ሺህ በላይ ወጣቶችን ለመደገፍ እንደሚሰራ ከቀናት በፊት ዘርፉን እንዲመሩ የተመረጡት ዶክተር እሌኒ ገብረ መድህን ገልጸዋል፡፡
መርሃ ግብሩ ከመንግሥታዊና ከግል ተቋማት በሚገኝ ገንዘብ አፍሪካውያን ወጣት የስራ ፈጣሪዎችን በእውቀት፣ ገንዘብና ምቹ የስራ ሁኔታ በመፍጠር የሚደግፍ ሲሆን ለቀጣዮቹ 10 ዓመታት የሚተገበር መሆኑን ቢቢሲ አስነብቧል፡፡
ድጋፉ የስራ ፈጣሪዎችን ከትምህርትና ከቢዝነስ ተቋማት ጋር የሚገናኙበትን ዕድልም የሚፈጥር ነው።
ዶክተር እሌኒ ገብረ መድህን እንደተናገሩት ይህ አፍሪካዊ ወጣትና ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎችን የሚደግፈው መርሃ ግብር እስከ 10 በሚደርሱ የአፍሪካ ሀገራት ማዕከላት ይኖሩታል።
በ10 ዓመታት ውስጥ ከ1 ሺህ በላይ ስራ ፈጣሪዎችን መደገፍና ‹‹ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ›› የሚሰራው መርሃ ግብሩ፣ ‹‹አንዳንዶቹ [ጀማሪ የስራ ፈጣራ ድርጅቶች] አንዳንዶቹ ደግሞ በጣም ትልልቅ ኩባንያ ይሆናሉ። አንዳንዶቹ ባሉበት ሆነው ሊቀጥሉ ይችላሉ። ግን ሃሳቡ ምንድን ነው ቢያንስ እነዚህን አንድ ሺህ ድርጅቶች ትልቅ ቦታ ለማድረስና ለመደገፍ ነው ዓላማው›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ አማካኝነት የሚሰበሰበው ገንዘብ ተከፋፍሎ ወጣት የስራ ፈጣሪ አፍሪካውያንን በሁለት መልኩ እንደሚደግፍ ዶክተር እሌኒ ተናግረዋል። መርሃ ግብሩ ‹‹የፈጠራ ስራ ድርጅቶችን የሚያለማ በአንድ በኩል ተቋም ይኖረዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ለሚለሙት [የፈጠራ ስራዎች] ገንዘብ የሚያበረክት›› አካል ይኖረዋል።
እንደ ፈረንጆቹ በ2022 መጀመሪያ ላይ ወደ ስራ የሚገባውን ይህን መርሃ ግብር፣ የመግሥትና የግል ተቋማት በጥምር በገንዘብ የሚደግፉበት ስርዓትን ይከተላል ተብሏል።