Sunday, September 22, 2024
spot_img

ከአዲስ መንግሥት ምሥረታ ማግሥት ‹‹የብሄራዊ መግባባት›› ድርድር ይጀመራል ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ መስከረም 21፣ 2014 ― ገዥው ፓርቲ ብልፅግና ለድርጅቱ አመራሮች ባሰራጨውና ውይይት ባደረገበት ሰነድ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ አዲስ መንግስት ካቋቋሙ በኋላ በቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ድርድርና ውይይት ለማድረግ ተዘጋጅተዋል ብሏል፡፡

የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን በኢትዮጵያ ለመገንባት በሚያዚያ 2010 ለውጥ ቃል በተገባው መሰረት ሁለት ረድፍ ያለው የተሀድሶ ፕሮግራም ለማድረግ ብልፅግና መዘጋጀቱን ዋዜማ ራድዮ ሰነዱን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ አንዱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ለማስፋት የሚወሰደው እርምጃ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን አዲስ በሚመሰረተው የፌደራልና የአካባቢ መንግስታት መዋቅር ውስጥ በማካተት ተሳትፏቸውን ማሳደግ የዲሞክራሲ ልምምድ ማድረግ ነው።

ሌላው እርምጃ በሀገሪቱ ያለመግባባትና የግጭት ጭምር ምክንያት በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከፖለቲካ ድርጅቶች ሲቪል ማህበራት ምሁራንና መገናኛ ብዙሀን የተሳተፉበት የብሄራዊ መግባባት ውይይት መጀመር ነው። በዚህ ውይይት ሕገ መንግስቱን ጨምሮ ሰንደቅ አላማ ፣ ብሄራዊ መዝሙር፣ ብሄራዊ በዓላት እና ሌሎችም ጉዳዮች ተነስተው መግባባት ላይ የሚደረሰበት ነው።

ሕገመንግስቱ ከቀዳሚ አጀንዳዎች መካከል እንደሚሆን ነገር ግን አጀንዳዎችን የመምረጥና ቅደም ተከተል የማስያዙ ስራ የድርድሩ አንድ አካል እንደሚሆን በሰነዱ ተብራርቷል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በአዲሱ መንግስት ለማሳተፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተፈለገው መጠን ማሳተፍ እንደማይቻልና ሌሎች ተሳትፎን ለማሳደግ የሚረዱ መድረኮች እንደሚመቻቹ የብልፅግና ሰነድ ያትታል።


ሰነዱ ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲደርስ መደረጉም ተሰምቷል፡፡ በሰነዱ ‹‹ምንም እንኳን ምርጫው ውጤታማ በሆነ መልኩ ቢካሄድም የተጀመረው ዴሞክራሲያዊ ሽጝርን የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጨማሪ እርምዎች መወሰድ አለባቸው፡፡ በርካታ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለፌደራልና ክልል ም/ቤቶች እጩ ማቅረብ ቢችሉም፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምክር ቤቶች ያላቸው ውክልና አነስተኛ ሆኗል፡፡ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ዝቅ ያለ ውጤት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕብረት አለመፍጠራቸውና ገዢው ፓርቲ በሥልጣን ላይ መሆኑ የሚሰጠው ጥቅም ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም ገዢው ብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ሽግግሩን ከማጠናከር አኳያ በተለያዩ መንገዶች የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ከፍ ማለት እንዳለበት ከልብ ተቀብሎታል” እንደሚል ተጠቅሷል፡፡  

በሰሞኑ የክልል ምክር ቤቶች ምስረታ ላይ አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መቀመጫና የተለያዩ ሹመቶችን እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፣ በመጪው ሰኞ በሚመሰረተው የፌደራል መንግስት ውስጥም የተወሰኑ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እንደሚደለደሉ ዘገባው ያመለክታል።

በመንግስት ምስረታ ማግስት እንደሚደረግ በሚጠበቀው የብሄራዊ መግባባት ድርድር ከመንግስት ጋር ጦርነት የገጠመው ሕወሓት ይሳተፍ እንደሆነ ስነዱ ያብራራው ነገር የለም ተብሏል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img