Sunday, November 24, 2024
spot_img

በጦርነቱ ምክንያት በአፋር ክልል የአንበጣ መከላከያ የአውሮፕላን ኬሚካል ርጭት ማካሄድ አለመቻሉን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ መስከረም 20፣ 2014 ― የአንበጣ መንጋ በአፋር ክልል እና በሶማሌ ክልል ሁለት ዞኖች መከሰቱን ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሚኒስቴሩ የዕፀዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ንጉሤ እንደተናገሩት የአንበጣ መንጋው በአፋር ክልል እና በሶማሌ ክልል ሲቲ እና ፋፈን ዞኖች ተከስቷል።በሶማሌ ክልል ሁለቱ ዞኖች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በሶማሊ ላንድ በኩል አድርጎ የገባ ሲሆን፤ አሁን ላይ የኬሚካል ርጭት በአውሮፕላን በተደራጀ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በአፋር ክልል ባሉ ወረዳዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በኩብኩባ ደረጃ ላይ መሆኑን የተናገሩት አቶ በላይነህ፣ መንጋው የተከሰተባቸው አካባቢዎች ከምሥራቅ አማራ ወረዳዎች ጋር የሚዋሰኑ በመሆኑ መንጋው የመዛመት አድሉ ሰፊ መሆኑን ተናግረዋል።መንጋው የባሰ ጉዳት እንዳያደርስ እና እንዳይዛመት በሰው ሀይል እና በመኪና የኬሚካል ርጭት የፌደራል መንግስት ከአፋር ክልል መንግስት ጋር በመቀናጀት በመካሄድ ላይ መሆናቸውን አቶ በላይነህ ገልጸዋል።

መንጋው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በቀላሉ ለመቆጣጠር በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት ማካሄድ ቢያስፈልግም በአካባቢው ጦርነት መኖሩ ስጋት መፍጠሩ ተገልጿል።የአውሮፕላን ርጭት ለማካሄድ አውሮፕላኑ የግድ ዝቅ ብሎ መብረር አለበት የሚሉት አቶ በላይነህ፣ ይሄን ለማድረግ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከኢትዮጵያ አየር ሀይል እና ከሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ጋር በመወያየት ላይ መሆናቸውንም ዳይሬክተሩ አክለዋል።

ይሁንና ዘንድሮ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከዚህ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ እና በቀላሉ በቁጥጥር ሰር ማዋል እንደሚቻል አቶ በላይነህ ተናግረዋል።በዘንድሮው የመኸር ወቅት በሰብል ልማት ስራው ላይ ከአንበጣ መንጋው በተጨማሪ የግሪሳ ወፍ ሌላኛው ስጋት መሆኑንም ዳይሬክተሩ መግለጻቸውን አል ዐይን ዘግቧል።የግሪሳ ወፍ የስምጥ ሸለቆን ተከትሎ በመንጋ የሚንቀሳቀስ ሰብል አውዳሚ የወፍ ዝርያ ሲሆን፤ ርጭቱን ለማከናወን የአውሮፕላን እና የኬሚካል ዝግጅቱ መጠናቀቁም ተገልጿል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img