Thursday, November 21, 2024
spot_img

የኢዜማው አቶ ግርማ ሠይፉ ሹመት በፓርቲያቸው አልጸደቀም ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ መስከረም 19፣ 2014 ― በአዲስ አበባ ካቢኔ ውስጥ ሹመት አግኝተው የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን እንዲመሩ የተሰየሙት የኢዜማ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት የአቶ ግርማ ሰይፉን ሹመት ፓርቲያቸው ገና እንዳላፀደቀው ተሰምቷል።

የከተማይቱ የካቢኔ አባላት በትላንትናው እለት ቃለ መሃላ በፈጸሙበት ወቅት በአካል አለመቅረባቸው የተነገረው አቶ ግርማ፣ ፓርቲያቸው ውሳኔውን ያላፀደቀው ለተመሳሳይ ጉዳዮች ውሳኔ ይሰጣል የተባለው የኢዜማ ጠቅላላ ጉባኤ ባለመካሄዱ ነው ተብሏል።

ከኢዜማ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ሰምቻለሁ ብሎ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር እንደዘገበውም፣ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን በመጪው ቅዳሜ እና እሁድ የሚካሄድ ይሆናል።

ኢዜማ “ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ የመስራት መርህ አለው” የሚሉት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፤ የአቶ ግርማ ሹመት በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ሳይጸድቅ፤ በአዲስ አበባ ካቢኔ ምስረታ ላይ መነገሩ “በመርህ ደረጃ የሚያመጣው ችግር የለም” ብለዋል።

ሆኖም አካሄዱን ግን “በአፈፃፀም ደረጃ ከፍተኛ ክፍተት ያለበት” ነው ብለውታል።

በጉዳዩ ላይ በኢዜማና በገዢው ብልፅግና መካከል የመረጃ ክፍተት እንደነበርም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል።

የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው የተመረጡት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች መካከል ከኢዜማው አቶ ግርማ ሠይፉ በተጨማሪ በካቢኔያቸው ያካተቷቸው የአብን ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ዩሱፍ ኢብራሂምን የመንግስት ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ኃላፊ አድርገዋል። አቶ ዩሱፍ ኢብራሂምም በተመሳሳይ በትላንትናው ቃለ መሃላ አፈጻጸም ሥርዐት ላይ እንዳልተገኙ ተነግሯል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img