አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ መስከረም 18፣ 2014 ― በካይሮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከቀጣይ ጥቅምት ወር ጀምሮ በጊዜያዊነት እንደሚዘጋ በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ መናገራቸውን ቢቢሲ ዐረብኛ ዘግቧል፡፡ ኤምባሲው ከሦስት እስከ ስድስት ወራት እንደሚዘጋ የተናገሩት አምባሳደሩ፣ ዋና ምክንያቱ ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
‹‹ኤምባሲው አንዳንድ ወጪዎችን ለመቀነስ በሚል ከጥቅምት ወር ጀምሮ ለሚቀጥሉት ከሦስት እስከ ስድስት ወራት የሚዘጋ ይሆናል›› ሲሉ ነው አምባሳደሩ የገለጹት፡፡
አምባሳደሩ የኤምባሲው መዘጋት በሶስቱ ሀገራት ማለትም በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል ካለው የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ጋር የሚገናኘው አንዳች ነገር እንደሌለም አስረድተዋል፡፡
ኤምባሲው ዝግ በሚሆንበት ወቅት የኤምባሲው ኮሚሽነር ጉዳዮቹን እንደሚከታተልም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ በሌላኛዋ የሰሜን አፍሪካ አገር በአልጀሪያ፣ አልጀርስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከቀጣይ ጥቅምት ወር ጀምሮ እንደሚዘጋ ኤምባሲው ማሳወቁ መነገሩ አይዘነጋም፡፡ ለአልጀርሱ ኤምባሲ መዘጋት የኮሮና ቫይረስ ያስከተለው ጉዳት የፈጠረው የገንዘብ እጥረት በምክንያትነት ተጠቅሶ ነበር፡፡