Sunday, October 6, 2024
spot_img

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ከ12 ዓመታት በኋላ ሊተገበር መሆኑ ተጠቆመ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ መስከረም 17፣ 2014 ― ላለፉት 12 ዓመታት ተሞክሮ ብዙም ርቀት ሳይሄድ ተቋርጦ የነበረው ብሔራዊ መታወቂያ ትግበራ ፕሮጀክት፣ የሙከራ ውጤታማነቱ በመረጋገጡ መተግበር ሊጀመር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ብሔራዊ መታወቂያን ትግበራ በሚመለከት ሰላም ሚኒስቴር በድረ ገጹ እንዳስታወቀው የብሔራዊ መታወቂያ ለሰላም፣ ለኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት፣ ለአገር ደኅንነት መልከ ብዙና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡

የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ዓርብ መስከረም 14 ቀን 2014 ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት እንዳስረዱት፣ ፕሮጀክቱ ከ12 ዓመታት በፊት ተጀምሮ እዚህ ግባ የሚባል ርቀት ሳይሄድ ተቋርጦ ነበር።

በሰላም ሚኒስቴር መሪነት ከሚመለከታቸው ተቋማት የጋራ ተሳትፎና በመስኩ ዕውቀቱ ባላቸው ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በተከናወኑ ተግባራት፣ በራስ አቅም ፍሬ አፍርቶ ስምንት በሚሆኑ የፌዴራል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሙከራ ትግበራ ተካሂዶ ውጤታማነቱ መረጋገጡን አስታውቀዋል።

እንደ ሚኒስተሯ ገለጻ፣ የውጤቱ ተጠቃሚ ከሆኑ ተቋማት አንዱ ከሆነው የባንክ ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ አስተባባሪነት ከ16 የባንኮች ፕሬዚዳንቶች ጋር ሥራው የደረሰበትን ደረጃና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት መካሄዱን አብራርተዋል።

በቀጣይ ስድስት ወራት 30 ሚሊዮን ዜጎችን የመመዝገብ ግብ በተያዘለት አቅጣጫ እንዲሳካ፣ ሁሉም ዜጎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img