Sunday, September 22, 2024
spot_img

ባንኮች የደንበኞቻቸውን ማንነት በጥልቀት የሚመዘግብ አዲስ መታወቂያ እንዲያዘጋጁ መታዛዘቸው ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ መስከረም 14፣ 2014 ― በፋይናንስ ዘርፍ ያለውን ውንብድና ለመቆጣጠር፣ የህገ ወጥ ገንዘብ ፍሰትን ለመከታተል እንዲሁም በተለያዩ የሽፋን ስሞችና የተጭበረበሩ ሰነዶች የሚደረገውን የገንዘብ ዝውውር ለማስቀረት ባንኮች አዲስ የባንክ መለያ መታወቂያ እንዲያዘጋጁ መታዘዛቸውን ተሰምቷል፡፡

ለዚህም ሁሉም የንግድ ባንኮች የደንበኞቻቸውን ማንነት እና ሙሉ መረጃ አደራጅቶ ሊይዝ የሚችል የየባንኮቹ የራሳቸው የደንበኛ መታወቂያ ካርድ እንዲያዘጋጁ ብሄራዊ ባንክ ትዕዛዝ ማስተላለፉ የተነገረ ሲሆን፣ ይህን ለመስፈፀም አጋዥ እንዲሆን ብሄራዊ ባንክ መመሪያ በማዘጋጀት ለባንኮች ባለፉት ቀናት እንዲደርስ አድርጓል፡፡

ባንኮች የደንበኞቻቸውን መረጃ አጣርቶ መረጃውን ለመቀመርና መታወቂያ ለመስጠት የ6 ወራት ግዜ ተሰጥቷቸዋል።

በቅርቡ ሁሉም ባንኮች በዚሁ መመሪያ አተገባበር ላይ ባደረጉት ስብሰባ ስራውን ለማጠናቀቅ የ6 ወር የግዜ ገደብ መቀመጡ በቂ አለመሆኑን በሀገሪቱ ግዙፍ ከሆነው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተወካዮች በስፋት መነሳቱም ነው የተነገረው፡፡

ይህ አዲሱ የብሄራዊ ባንክ መመሪያ ደንበኞች ወደ ባንክ ሄደው ሂሳብ ሲከፍቱ ከሚሞሏቸው መረጃዎች ተጨማሪ ዝርዝር የደንበኛን መረጃ ጭምር በማከል የሚዘጋጅ መሆኑን መመሪያው ጠቅሷል።

ከዚህ ቀደም ባንኮች ደንበኞቻቸውን የሂሳብ ደብተር ሲከፍቱ ይጠየቁ ያልነበሩ መረጃዎች በአዲሱ አሰራር እንዲካተቱም መደረጉ ሲነገር፣ ለአብነት ያህል አንድ ደንበኛ የባንክ ደብተር የሚከፍትበት ምክንያትን እንዲያስረዳ የሚጠየቅ፣ ከዚያም ባሻገር የእናት ስም እና ተጨማሪ የቤተሰብና የግል መረጃዎች እንዲሰፍሩ እንዲደረግም ያዛል።

ብሄራዊ ባንክ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ቀደም ሲል የግለሰቦችን ሂሳብ ለማንቀሳቀስ እንደ ማመሳከሪያ ሆኖ ሲያገለግል የቆየውን የቀበሌ መታወቂያ አንድ ግለሰብ በተለያዩ አካባቢዎች የመያዝ እድል ስላለው አስተማማኝ መረጃ ማሰባሰብ አስቸጋሪ መሆኑ ስለታመነበት ነው ተብሏል።

ይህ አዲሱ በብሄራዊ ባንክ በኩል እንዲተገበር መመሪያ የተላለፈበት የባንኮች ‘’የደንበኛ መታወቂያ’’ በአንድ ባንክ ውስጥ የተከፈቱ የአንድ ግለሰብን ከሁለት በላይ የባንክ ሂሳቦችን በአንድ በማጣመር ተደራራቢ የሆኑ የደንበኞችን መረጃዎች ማስቀረት አላማው እንዲሆነ ታሳቢ ተደርጓል።

በቀጣዮች ደግሞ እየታሰበ ያለው በሀገር አቀፍ ደረጃ ብሄራዊ የመታወቂያ አገልግሎት ተግባራዊ መደረግ ሲጀምር በአንድ ባንክ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የሂሳብ ደብተሮችን ከማስተሳሰር ባሻገር፤ አንድ ደንበኛ በተለያዩ ባንኮች ያሉትን የሂሳብ ደብተሮች በማስተሳሰር በቀላሉ መረጃን ማደራጀት እንዲቻልም ታስቧል።

ይህን ሂደት በፍጥነት ለማጠናቀቅ ብሄራዊ ባንክ ከሰላም ሚኒስቴር እና ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም የዘገበው ዋዜማ ራድዮ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img