Sunday, October 6, 2024
spot_img

አዲስ የሚመሠረተው መንግሥት ፓርላመንታዊ ሆኖ ይቀጥላል ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ መስከረም 13፣ 2014 ― ከአስር ቀናት በኋላ መስከረም 24 የሚመሠረተው አዲሱ የአፌዴሪ መንግስት እንደ ከዚህ ቀደሙ ፓርላመንታዊ ሆኖ እንደሚቀጥል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ መናገራቸውን አል ዐይን ዘግቧል፡፡

ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆኑ የመንግስት መሪዎች የገዥው ፓርቲ ሊቀመንበር የነበሩ መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፣ አሁን ግን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት በመሆናቸው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉ አስተያየቶች መኖራቸውን አንስቷል፡፡

በጉዳዩ ላይ የተናገሩት ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፣ የአንድን ሀገር ስርዓት በአንድ ጊዜ ተነስቶ ከፓርላመንታዊ ወደ ፕሬዝዳንታዊ መቀየር እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩ ሰፊ ስራ እና ውይይት እንደሚጠይቅ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ከምንም በላይ ደግሞ እንደዚህ አይነት ጉዳይ ሕገ መንግስታዊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ዶክተር ቢቂላ የመንግስትን ስርዓት ፕሬዝዳንታዊ ወይም ፓርላመንታዊ የማድረግ ሃሳብ የሕዝብ በመሆኑ ውይይት እንደሚጠይቅ ያነሱ ሲሆን፤ በሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ መታየት ያለባቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉና ሀገርን የማሻሻሉ ስራ ቀን የሚቆረጥለት ባለመሆኑ ወደፊት ብዙ ለውጦች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ገዥው ፓርቲ ብልጽግና አብላጫ ድምጽ ማግኘቱ ይፋ መደረጉ ይታወቃል፡፡

የፎቶ ምንጭ፡ አል ዐይን

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img