አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ መስከረም 12፣ 2014 ― የኢትዮጵያ ልዑካንን ጨምሮ ከመላው ዓለም የተውጣጡ መሪዎች በተገኙበት 76ኛው የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ፤ በተለያዩ አገራት ያሉ ግጭቶች ጉዳይ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም ሌሎችም ወቅታዊ እና አንገብጋቢ ርዕሰ ጉዳዮች ተነስተዋል።
በጉባኤው ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት የተነሱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲተባበር ጠይቀዋል።
በአሜሪካ፣ ኒው ዮርክ እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ባይደን ‹‹እንደ ኢትዮጵያ እና የመን ባሉ አገራት የተነሱ ግጭቶችን ከመፍታት ወደኋላ ማለት የለብንም›› ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ጦርነት ውስጥ የገቡ ወገኖች ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመጡ ለማድረግ በሚደረግ ጥረት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተስፋ እንዳይቆርጥም ጠይቀዋል።
‹‹በጦርነት ሳቢያ ረሃብ እየተነሳ ነው። እጅግ አሰቃቂ ጥቃት እየተፈጸመ ነው። የንጹሀን ሰብአዊ መብት እየተገፈፈ ነው። መድፈር እንደ ጦር መሣሪያ እየዋለ ነው›› ሲሉም በጉባኤው ንግግር አድርገዋል።
መንግሥታቸው ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በመሆን አሁን እየተስተዋለ ያለውን ሰቆቃ ለመግታት ብሎም ሰላም ለማምጣት እንደሚሠራም ቃል ገብተዋል።
አስር ወራት ባስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ብዙ ሺዎች ሲሞቱ፤ በርካቶች የረሃብ አፋፍ ላይ እንደሚገኙ ይነገራል፡፡