Sunday, September 22, 2024
spot_img

ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር የሚለው ቡድን ከሰሞኑ አገር ቤት መመለሱ የተነገረው አዛዡ ከሥልጣን ከተነሳ አንድ ዓመት አስቆጥሯል አለ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ መስከረም 12፣ 2014 ― በመንግስት ሸኔ የሚባለውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን ከሰሞኑ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ለሰላማዊ ትግል ወደ አገር ቤት መመለሱ የተነገረለት የደቡብ ዞን አዛዥ ነበር የተባለው ጎሊቻ ዴንጌ በጤና እክል ምክንያት ከጦር አዛዥነቱ ከተነሳ ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆነ አሳውቋል፡፡

እንደ ቡድኑ ከሆነ በዚሁ ምከንያት የጎሊቻ ምክትል የነበረው ግለሰብ የደቡብ ዞን እንዲመራ መሾሙን ቡድኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ቡድኑ ከዚህ በተጨማሪም ጎሊቻ ዴንጌ የጤና መሻሻል ካሳየ በኋላ በተደጋጋሚ ወደ ሥራው እንዲመለስ የቀረቡለትን ጥያቄዎች ሳይቀበል ቀርቷል ብሏል።

ለሶስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ የትጥቅ ትግል አካሂዷል የተባለለት ጎሊቻ፣ አዲስ አበባ መግባቱን ተከትሎ የሰላማዊ ትግል ለማካሄድ መወሰኑን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የቀድሞ የኦሮሞ ነጻነት ጦር የደቡብ ዞን አዛዥ ጎሊቻ ዴንጌ ከቡድኑ ተለይቶ ወደ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ በኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

ጎሊቻ ዴንጌ ወደ አገር ቤት ከተመለሰ በኋላ አግንቼዋለሁ ያለው ቢቢሲ፣ በድርጅቱ ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት እና በቅርቡ ቡድኑ ከሕወሓት ጋር አብሮ ለመስራት መስማማቱ ድርጅቱን ጥሎ እንዲወጣ ምክንያት እንደሆነው ነግሮኛል ብሎ ዘግቧል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስርት ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ የኦነግ ሠራዊት አገር ቤት ሲገባ ‹‹እኔ የቁም እስረኛ ነበርኩ›› የሚለው ጎሊቻ፤ በቡድኑ ተገዶ ለመገናኛ ብዙኃን ይናገር እንደነበረ ጭምር መግለጹ ተመላክቷል፡፡

የደረሰብኝ ጫና ላለፉት 27 ዓመታት ከነበርኩበት የትጥቅ ትግል እንድወጣ አድርጎኛል የሚለው ጎሊቻ፤ ‹‹አካሄድ ላይ አልተግባባንም። ከፍተኛ ጫና በእኔ ላይ አሳድረዋል። የግድያ ሙከራም አድርገውብኛል። አሁን ላይ እየተካሄደ ያለው ትግል እና አመራር ትክክል አይደለም። ባለፉት ሦስት ዓመታት ይህ መታደስ አለበት ብዬ ስናገር ነበር›› ማለቱንም የዜና ወኪሉ አስነብቧል፡፡
ጎሊቻ ከሚመራው ጦር ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የቦረና አገር ሽማግሌዎች እንዲያሸማግሏቸው ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር የሚለው ቡድን በአሁኑ ጊዜ በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ በሚገኙ አካባቢዎች በስፋት እንደሚንቀሳቀስ ይነገራል፡፡ ይህ ቡድን በሚንቀሳቀስባቸው ስፍራዎች የመንግሥት ባለስልጣናትን ጨምሮ ንጹሃን ዜጎችን በመግደል በተደጋጋሚ ይወቀሳል። የጉጂ እና የቦረና አባ ገዳዎችም ‹‹ሸኔ የኦሮሞ ጠላት ነው›› ሲሉ አውጀዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img