አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ መስከረም 10፣ 2014 ― የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ግጭት እንዲራዘም፣ ሰብአዊ ርዳታ እንዳይደርስ እና ተኩስ አቁም እንዳይደረግ መሰናክል በመሆን ተጠያቂ ናቸው ያሏቸው አካላት ላይ የገንዘብ ዝውውር እና የጉዞ ማዕቀብ እንዲጣል የሚያደርግ ማዕቀብ የአገሪቱ ግምጃ ቤት ተፈጻሚ እንዲያደርግ ማዘዛቸው ይታወቃል፡፡
የአሜሪካ መንግስት እዚህ ውስጥ አሉበት ብሎ ከዘረዘራቸው መካከል የሆነው የአማራ ክልላዊ መንግስት ክልል የአሜሪካ የዕቀባ ትዕዛዝ ውስጥ መካተቱ አሳሳቢ መሆኑን መግለጹን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡
ክልሉ ጨምሮም የአሜሪካ መንግሥት እና ግምጃ ቤቱ በሚያደርጉት ምርመራ እንደሚተባበር ያስታወቀ ሲሆን፣ ‹‹የአማራ ሕዝብ ወደ መኖሪያው ከመጡ ወራሪዎች እና ወንጀለኞች ራሱን እየተከላከለ ነው›› ማለቱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በአሜሪካ ማእቀብ ሥሙ የተጠቀሰው ሌላኛውና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት በበኩሉ ከሰሞኑ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የፈረሙበት ማእቀብ ተፈጻሚ እንዲሆን እሠራለሁ ሲል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ይህንኑ የአሜሪካን ማእቀብ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ለባይደን ግልጽ ደብዳቤ የጻፉ ሲሀን፣ በማእቀብ ስሙ የተጠራው የኤርትራ መንግስት ግን ይህ ዘገባ እስከተሰናዳበት ሰአት ድረስ ያለው ነገር የለም፡፡