አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ መስከረም 8፣ 2014 ― የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ግጭት እንዲራዘም፣ ሰብአዊ ርዳታ እንዳይደርስ እና ተኩስ አቁም እንዳይደረግ መሰናክል በመሆን ተጠያቂ ናቸው ያሏቸው አካላት ላይ የገንዘብ ዝውውር እና የጉዞ ማዕቀብ እንዲጣል የሚያደርግ መመሪያ ላይ መፈረማቸውን ይታወቃል፡፡
ማዕቀቡን የመጣል ኃላፊነት የተሰጠው የዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት እየተከታተለ ተግባራዊ እንዲያደርግ የታዘዘ ሲሆን፣ ማዕቀቡ ይመለከታቸዋል የተባሉት አካላትም ከጥቅምት ወር 2013 አንስቶ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ተሳታፊ የሆኑ ናቸው፡፡
እንደ ፕሬዝደንቱ መግለጫ፣ ማዕቀቡ የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት፣ የኤርትራ መንግሥት፣ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና የአማራ ክልላዊ መንግሥት ናቸው፡፡
ባይደን በፈረሙት ማዕቀብ የሚካተቱ ባለሥልጣናት ሊገጥማቸው የሚችሉ ነገሮች ቤተሰቦቻቸው እና ልጆቻቸውንም ይመለከታል ተብሏል።
ዋይት ሐውስ እንዳወጣው መግለጫ ከሆነ ማዕቀቡ የሚነካቸው ግለሰቦች በአሜሪካ ንብረት ካላቸው እንዳይንቀሳቀስ ገደብ የሚጣልበት ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የማእቀቡ ድንጋጌ ማንኛውም በአገሪቱ የሚገኝ ግለሰብ ማዕቀቡ ከተጣለበት ግለሰብ ጋር በኢንቨስትመንት መገናኘትም ሆነ ንብረቱን መግዛት ያግዳል፡፡ አያይዞም በአገሪቱ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ለግለሰቡ ገንዘብ ማበደር እንደማይችሉም የተጠቀሰ ሲሆን፣ እግዱ የተጣለበት ሰው ማንኛውም ገንዘብ እንዳያዘዋውርም ከልክሏል፡፡
በሌላ በኩል ማእቀቡ የሚጣልባቸው ባለሥልጣናት እና ግለሰቦች የሚቀመጠው እግድ ከራሳቸው በተጨማሪ ቤተሰቦቻቸው እና ልጆቻቸውንም ይመለከታል የተባለ ሲሆን፣ የአሜሪካ ዜግነት የሌላቸው ማዕቀቡ የሚመለከታቸውን ሰዎች ከሀገር ማስወጣትንም ሊጨምር እንደሚችል ተጠቅሷል።
ማዕቀቡ ላይ የፈረሙት ጆ ባይደን፣ ማዕቀቡ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካ ቀንድን ሠላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋት ለአደጋ ያጋልጣል በሚል መሆኑን በመግለጫቸው አሳውቀዋል።
በተለይም በአካባቢው ተስፋፋ ያሉት ግጭት፣ አስከፊ በደሎች፣ የመብት ጥሰቶች እና ብሔር ነክ ግጭቶች፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲሁም የሰብአዊ ርዳታ እንቅስቃሴን ማስተጓጎል የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ደኅንነት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ያልተለመደ እና ልዩ የሆነ አደጋ ደቅኗልም ብለዋል።