Monday, October 7, 2024
spot_img

ኢትዮጵያ እና ኤርትራን አሸማጋዩ አረፉ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ መስከረም 8፣ 2014 ― ከ20 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተፈረመውን የአልጀርስ ስምምነት አሸማጋዩ የቀድሞው የአልጄሪያ ፕሬዝዳንት ዐብደልአዚዝ ቡቴፍሊካ ከረዥም ጊዜ ሕመም በኋላ በ84 ዓመት እድሜያቸው አርፈዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በታኅሣሥ ወር 1993 በአገራቸው መዲና አልጀርስ በወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ መለስ ዜናዊ እና በኤርትራው ኢሳይያስ አፈወርቂ መካከል የተፈረመውን ስምምነት አስፈጽመዋል፡፡

ቡቴፍሊካ ከ1940 እስከ 1950ዎቹ አገራቸው አልጄሪያን ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ለማላቀቅ በተደረገው ጦርነት ውስጥ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል በሚል ይታወሳሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በ1966 የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት የነበሩት ቡቴፍሊካ የፍልስጤም መሪ የነበሩትን ያሲር አራፋት ለተባበሩት መንግሥታት ንግግር እንዲያደርጉ የጋበዙበት ሁኔታ ታሪካዊ በሚል ይጠቀሳል፡፡

በሌላ በኩል ቻይና የተባበሩት መንግሥታት መቀመጫ ሊኖራት እንደሚገባ በመሟገታቸው እንዲሁም በወቅቱ በደቡብ አፍሪካ የነበረውን የአፓርታይድ አገዛዝን በይፋ በመቃወማቸውም ቡቴፍሊካ ይታወሳሉ። ቡቴፍሊካ ለኔልሰን ማንዴላ ወታደራዊ ሥልጠና በመስጠታቸውም ይታወቁ ነበር።

በ1991 የ200 ሺህ ያህል ሰዎችን ሕይወት እንደቀጠፈ በሚነገረው የእርስ በእርስ ጦርነት መገባደዱን ተከትሎ በመጣው ወታደራዊው ግፊት ለፕሬዝዳንትነት የበቁ ሲሆን፣ ለ20 ዓመታት ገደማ ከመሩ በኋላ ለአምስተኛ የሥልጣን ዘመን ለመወዳደር መቅረባቸው ለከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ ዳርጓቸውም ነበር።

ቡቴፍሊካ በ2000 የፕሬዘዳንትነት ዘመንን ለሁለት ጊዜ የሚገድበውን የአልጄሪያን ሕገ-መንግሥት በማሻሻል ለተጨማሪ ሁለት የሥልጣን ዘመናት ቆይታቸውን አራዝመዋል።
በመቀጠልም የአረብ አብዮት በመላው ሰሜን አፍሪካ ሲነሳ ቡተፍሊካ ሕዝባዊ ድጎማዎችን በፍጥነት ያሳደጉ ሲሆን ለረዥም ዓመታት የቆየውን የአልጄሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንስተው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ በፈረንጆቹ 2005 በስትሮክ ከተመቱ በኋላ ንግግር እና እንቅስቃሴ ማድረግ ላይ ከፍተኛ እክል ስላጋጠማቸው በአደባባይ እምብዛም አይታዩም ነበር።

ለመጨረሻ ጊዜ ለሕዝብ የታዩትም ከአራት ዓመት በፊት በአልጄርስ የተገነባውን የባቡር ጣቢያ እና እድሳት ተድርጎለት የነበረው የኬቼዋ መስጊድን ባስመረቁበት ወቅት ሲሆን፣ ይህም በስትሮክ ከተመቱ ከአራት ዓመት በኋላ ነበር።

በሕመም ላይ የነበሩት ፕሬዝዳንቱ ለአምስተኛ የሥልጣን ዘመን እንደሚወዳደሩ ሲሰማ መላው አልጄሪያ በአመጽ ተቀጣጥላ፣ ታይቶ የማይታወቅ ነው በተባለ መልኩም በአገር አቀፍ ደረጃ በየሳምንቱ ሰላማዊ ሰልፎች ይደረጉ ነበር። ይህንን ተከትሎም ምርጫውን ለሌላ ጊዜ በማስተላለፍ ብሎም በአንድ ዓመት ውስጥ ሥልጣን ለመልቀቅ ቃል ከገቡ በኋላ ቡቴፍሊካ ከሥልጣን ወርደዋል። ይህም አልጄሪያዊያን ቡቴፍሊካን ለመጨረሻ ግዜ ያዩበት ሆኖ አልፏል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img