አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ መስከረም 8፣ 2014 ― ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች መስከረም 20 ለሚያካሂደው ምርጫ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ እንደገለጹት በተለያዩ ምክንያት ምርጫ ሳይካሄድባቸው በቀሩት በሶማሌ፣ የሐረሪ፣ የቤንሻንጉል፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልልና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አንዳንድ አካባቢዎች ቦርዱ በያዘው መርሃ-ግብር እንደሚካሄድ ተናግረዋል። ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅትም ከወዲሁ ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው የገለጹት፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ በዕለቱ ከምርጫው ጋር ጎን ለጎን አብሮ እንደሚካሄድ የጠቆሙት ሶሊያና፣ ሕዝበ ውሳኔ በኮንታ፣ በምዕራብ ኦሞ፣ በቤንቺ ሸኮ፣ በከፋ፣ በዳውሮ ፣ በሸካ ዞኖች የሚካሄድ መሆኑን አስታውሰዋል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ነው፡፡
የፎቶ ምንጭ፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት