Sunday, September 22, 2024
spot_img

በ25 ሚሊዮን ብር 5 መኪና ለኃላፊዎቹ የገዛው ኢቢሲ ከሠራተኞቹ 40 ሚሊዮን ብር መቁረጡ ቅሬታ አስነሳ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ መስከረም 8፣ 2014 ― የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ሠራተኞች ለመከላከያ ሠራዊት የአንድ ወር ደሞዝ መለገስ ግዴታችሁ ነው መባላቸው ቅሬታን አስነስቷል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት ከሆነ የዝቅተኛ ደሞዝ ተከፋዮችን ባላገናዘበ መልኩ የአንድ ወር ደሞዝ ሊወሰድ ነው ሲሉ ነግረውኛል ብሎ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ አስነብቧል፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ‹‹የኛን የደሀዎቹን ደሞዝ ከሚወስዱ ለአመራሮች ቅንጡ መኪና የተገዛበትን 25 ሚሊዮን ብር እና ለተለያዩ ወጪዎች የሚጠቀሙትን ገንዘብ መጠቀም ይችሉ ነበር›› ሲሉ መናገራቸው ነው የተመላከተው፡፡

ብሔራዊ ጣቢያው የ2021 ምርት የሆነ ሀዮንዳይ ቱክሰን የተባለ፣ የአንዱ ዋጋ አምስት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ዘመናዊ መኪና ለአምስት አመራሮች መግዛቱ ሲነገር፣ በጥቅሉ ግዥው 25 ሚሊዮን ብር መፍጀቱንና ይህም አሁን አገሪቷ ካለባት የውጭ ምንዛሬ እና የበጀት ዕጥረት አኳያ ቅንጡ መኪና መግዛት የሚኖርበት አይመስለንም ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልጸዋል።

ለመከላከያ ሠራዊት እና ለተፈናቃዮች ገንዘብ እንደሚያስፈልግ እየታወቀ፣ ተቋሙ መሠረታዊ ግብዓቶች ዕጥረት እያለበት፣ እንዲሁም ለመደበኛ ሠራተኛው ለሥራ የሚያስፈልገው የትራንስፖርት አገልግሎት ባልተሟለበት ሁኔታ ለአመራሮች የተገዛው እጅግ ውድ መኪና ቅር አሰኝቶናል ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በጷጉሜ ወር ላይ በኢትዮጵያ ሆቴል በተደረገ ስብሰባ የተቋሙ ሠራተኞች በ2014 አንድ ዓመት ውስጥ የአንድ ወር ደሞዛቸውን እንዲሰጡ ግዴታ ተጠሎባቸዋል። ከፍተኛ ደሞዝ ተከፋዮችን ብቻ ያካተተ ስብሠባ በኢትዮጵያ ሆቴል ተካሒዶ ነበር የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ ውሳኔው ያለውን የኑሮ ውድነት እና ዝቅተኛ ደሞዝ ተከፋዮችን ያላገናዘበ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ጋዜጣው ስማቸውን ያልጠቀሳቸው የአራት ሺሕ ብር ደሞዝተኛ ናቸው የተባሉ እና ሦሰት ልጆች ያላቸው አንድ የተቋሙ ሠራተኛ፣ የቤት ኪራይ 2 ሲሕ 500 ብር እንደሚከፍሉ ቢናገሩም፣ ምንም ተሰሚነት ሳያገኙ የአንድ ወር ደሞዝ መስጠት የማይችል ካለ ተቋሙን ለቆ ይውጣ በሚል የግዴታ ልገሳ አድርጉ መባላቸውን ገልጸዋል። ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ መደረግ እንዳለበት እናምናለን የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ ድጋፉ በበጎ ፈቃድ መሆን እደነበረበት ነው ያመለከቱት፡፡

በጉዳዩ ላይ ጥያቄውን በመያዝ ወደ ኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ንጉሴ ምትኩ (ዶ/ር) ጋር ደውያለሁ ያለው ጋዜጣው፣ ጉዳዩን ከሰሙት በኋላ ምላሽ ሳይሰጡ ስልኩን አቋርጠውታል ሲል አስነብቧል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img