አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ መስከረም 8፣ 2014 ― የጉጂ አባ ገዳዎች በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀስ የሚነገረው ታጣቂው ቡድን ‘ሸኔ’ የኦሮሞ ጠላት ነው ሲሉ አውጀዋል፡፡
አባገዳዎቹ መንግሥት ሸኔ የሚለው እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር እያለ የሚጠራው ቡድን ‘የኦሮሞ ጠላት ነው’ ሲሉ የፈረጁት በቡድኑ በርካታ ንጹሃን ዜጎች በመገደላቸው ነው ብለዋል።
ባህላዊው መሪ ታጣቂው ቡድን ላይ ውግዘት ያስተላለፉት ‹‹ኦሮሞ ሆኖ ኦሮሞን የሚገድል ጠላት ነው›› በማለት እንደሆነ የጉጂ አባ ገዳ ጂሎ ማንዶ ነግረውኛል ብሎ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት በጉጂ ሕይወት እጅጉን ፈታኝ ሆኗል የሚሉት አባ ገዳ ጂሎ፤ ‹‹የኦሮሞ ነጻነት ጦር ለኦሮሞ ሕዝብ ነው የምታገለው ይላል። ለኦሮሞ የሚታገ ከሆነ ኦሮሞን መግደል›› እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡
እንደ አባ ገዳ ጂሎ ማንዶ ከሆነ በሁለቱ የጉጂ ዞኖች ማለትም በጉጂ ዞን እና በምዕራብ ጉጂ ዞን ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ2 ሺሕ በላይ ንጹሃን ሰዎች ተገድለዋል፡፡
ከሦስቱ የጉጂ አባ ገዳዎች መካከል አንዱ የሆኑት አባ ገዳ ጂሎ፤ ‹‹እኛ ስለፖለቲካው አይደለም። ኦሮሞ ኦሮሞን መግደል የለበትም። ኦሮሞን የሚገድል ጠላታችን ነው ያልነው። ለኦሮሞ ነው የምንታገለው ብለው ሕዝቡን እየጨረሱ ነው›› ብለዋል።
አባ ገዳው ‹‹በቅርቡ እንኳን ዱግደ ዳወ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በአንድ ቤት ውስጥ 13 ሰዎች ከገደሉ ሳምንት አልሆም›› ሲሉ አስታውሰዋል፡፡
አባ ገዳው ጨምረውም፤ ‹‹መንግሥትን የሚፈልግ ከሆነ ከመንግሥት ጋር መዋጋት ነው እንጂ›› ሕዝብ ለምን ይጨርሳል ሲል ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡
አባ ገዳው የመንግሥት ኃይል በተመሳሳይ ንጹሃንን ይገድላል ሲሉም እንደሚከሱ ዘገባው አመልክቷል፡፡
የጉጂ አባ ገዳዎች ከዚህ ውሳኔ ደረሱት ሕዝብ ወደ አደባባይ ወጥቶ የጉጂን ሕዝብ እየጨረሰ ያለውን ታጣቂ ቡድን ሥርዓት አስይዙ ብሎ ስለጠየቃቸው መሆኑን ገልጸዋል።
አባ ገዳው ከዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ አንዳችም የመንግሥት ጫና እንዳልገጠማቸው የተናገሩ ሲሆን፣ ‹‹እኛ መንግሥትንም አንፈልግም፤ መንግሥት ቢኖር ኖሮ ይህን ያክል ሕዝብ ያልቅ ነበር?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡
በጉጂ ዞኖች ባለው የፀጥታ ችግር ሕዝቡ የዕለት ሥራውን ማከናወን እንደተሳናው ያስረዱት አባ ገዳው፣ ‹‹ሕዝቡ የሚሄድበት ግራ ገብቶታል። ገበሬው አያርስም፣ ነጋዴውም መነገድ አልቻለም። ለቅሶ መድረስ አልቻለም›› በማለት ውሳኔው ለአካባቢው ሰላም ያመጣል ብለው ያምናሉ።
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ የቦረናው አባ ገዳ ታጣቂው ቡድን የሕዝብ ጠላት ነው ብለው ከፈረጁ በኋላ በቦረና ሰላም መስፈኑንም አስታውሰዋል፡፡
በኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ አባ ገዳዎች በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ሲሆኑ፣ የሚያስተላልፉትም መልዕክት ተቀባይነት ያለውና ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆኑ ይታወቃል፡፡