አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ መስከረም 7፣ 2014 ― አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ የያዘችው ፖሊሲ አስደንጋጭ እና ከሰብዓዊ እርዳታ ያለፈ እንደሆነ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ አስታውቀዋል።
የፕሬዝዳንቱ አስተዳደር በሕወሃት ላይ ለምን ጠንካራ አቋም እንዳልያዘ ግልጽ እንዳልሆነ የጠቀሱት ዐቢይ፣ ኢትዮጵያ ግን ከሕወሃት የደቀነባትን አደጋ ግን በአሸናፊነት ትወጣዋለች ብለዋል።
አልሸባብን በመዋጋት የአሜሪካ አጋር የሆነችው ሀገሬ፣ ሌላ አሸባሪ በቀጠናው ላይ ስጋት ሲደቅን አጋርነቷን ታሳያለች ብለው ይጠብቁ እንደነበር ዐቢይ የገለጹ ሲሆን፣ የአሜሪካ ውጭ ፖሊሲ በዓለማቀፍ የፖሊሲ ወትዋቾች ተጽዕኖ ስር መውደቁንም ጠቁመዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት የተኩስ አቁም ንግግር ባስቸኳይ ካልተጀመረ የአሜሪካው ግምጃ ቤት መጠነ ሰፊ ማዕቀቦችን እንዲጥል በዛሬው እለት ትዕዛዝ ማስተላለፉ አይዘነጋም።