Monday, November 25, 2024
spot_img

በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ ታጣቂዎች በሰነዘሩት ጥቃት ሁለት አርሶ አደሮችን መገደላቸውን የልዩ ወረዳው አስተዳደሪ ገለጹ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጳጉሜን 1፣ 2013 ― በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ ታጣቂዎች በሰነዘሩት ጥቃት ሁለት አርሶ አደሮችን መገደላቸውን አቶ ወገኔ ብዙነህ ገልፀዋል።

ጥቃቱ ዛሬ ረፋድ ላይ የተፈጸመው በልዩ ወረዳው ጀሎ በተባለ የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው።

አርሶ አደሮቹ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው በእርሻ ስራቸው ላይ በነበሩበት ወቅት መሆኑን የጠቀሱት አስተዳዳሪው፣ በተለይም ከሟቾቹ አንደኛው ከግብርና ስራቸው ጎን ለጎን በቀበሌው መስተዳድር ውስጥ በምክትል ሊቀመንበርነት ሲያገለግሉ የነበሩ ናቸው ብለዋል።

የአማሮ ኮሬ እና የጉጂ አሮሞ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ በሀዋሳ ከተማ ባካሄዱት የሰላምና የእርቅ ኮንፍረንስ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል የተፈጠረውን ስጋትና ጥርጣሬ በመቅረፍ በጋራ ለመስራት ከሚያስችላቸው ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

የዛሬው ጥቃት በሀዋሳው የሰላምና የእርቅ ስምምነት መሰረት በቀጣይ ሁለቱ ሕዝቦች በሚጎራበቱባቸው ቀበሌያትና መንደሮች ተመሳሳይ የእርቅ ሂደቶችን ለማከናወን በተያዘው ዕቅድ ላይ አሉታዊ ተፅኖ ሊያሳድር ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል።

ጥቃቱ የእርቅ ሂደቱ አንዳይሳካ በማይፈልጉ ቡድኖች ሆን ተብሎና ታቅዶ የተፈጸመ ነው ያሉት የልዩ ወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ወገኔ በአሁኑ ወቅት ልዩ ወረዳው ከምዕራብ ጉጂ ዞን የፀጥታ አካላት ጋር መረጃ በመለዋወጥ ጥቃት አድራሾቹን ለመያዝ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል መባሉን የዘገበው ዶይቸ ቨለ ነው።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img