Sunday, September 22, 2024
spot_img

የአማራ ታጣቂዎች በሁመራ በሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ላይ ዘግናኝ ጥቃት መፈፀማቸውን በምርመራ አረጋግጠናል ሲሉ ቴሌግራፍ እና ሲ.ኤን.ኤን ዘገቡ

– የአማራ ክልል የፀጥታና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰማ ጥሩነህ ‹‹በተባሉት አካባቢዎች ችግር ደርሶብኛል ብሎ ወደ ቢሮዬ ሪፖርት ያደረገ አንድም ትግርኛ ተናጋሪ የለም›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጳጉሜን 1፣ 2013 ― የአማራ ታጣቂዎች በሁመራ በሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ላይ ዘግናኝ ጥቃት መፈፀማቸውን በምርመራ አረጋገጥናል ሲሉ የእንግሊዙ ቴሌግራፍና የአሜሪካው ሲ.ኤን.ኤን ዘግበዋል፡፡

እንደ ቴሌግራፍ ዘገባ ከሆነ ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ያደረሱት በሁመራ ከተማ ሲሆን፣ ይህንኑ በርካታ የዐይን እማኞች አረጋግጠውልኛል ብሏል፡፡

እነዚሁ ታጣቂዎች በከተማው ቤት ለቤት እየዞሩ ካገኟቸው መካከል አንዳንዶቹን የትግራይ ተወላጆች እጅና እግራቸውን ቆራርጠው መግደላቸውን ተዘግቧል፡፡

ሃምሳ ሺሕ ነዋሪዎች አሉባት በምትባለው ሑመራ ከተማ ሐምሌ 8 ቀን የትግራይ ተወላጆችን እጣ ፋንታ ለመወሰን የአማራ ታጣቂዎች በከተማው ዋና አዳራሽ ተሰብስበው እንደነበር ያመለከተው ቴሌግራፍ፣ በዚሁ ስብሰባ ወቅት ከከተማው መጽዳት አለባቸው መባሉን ከተሳታፊ መስማቱንም አስነብቧል፡፡

ይህንኑ ተከትሎም ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻ ወደ ሱዳን ሸሽተው ካመለጡ እና በዚያው ቦታ አግኝተው ከተደበቁት ውጪ በከተማው ሳይያዝ የቀረ የትግራይ ተወላጅ አልነበረም ተብሏል፡፡

በከተማው ይገኙ የነበሩ ሕፃናት እና አዛውንቶች ጨምሮ የትግራይ ተወላጆች ወደ ሦስት ማጎሪያዎች እንዲከተቱ ተደርገዋል የተባለ ሲሆን፣ በዘገባው ከነዚህ ማጎሪያዎች የትግራይ ተወላጅ አለመሆኑን አሳምኖ ማምለጡ የተጠቀሰ አንድ ግለሰብ፣ እርሱ ነበርኩበት ባለው ማጎሪያ 250 ሰዎች ይገኙ እንደነበርና ታጣቂዎቹ በየለቱ በሥፍራው ካሉት ላይ እየቀነሱ አዳዲስ ሰዎች ያመጡ ነበር ማለቱ ተመላክቷል፡፡ እንደ ግለሰቡ ከሆነ ታጣቂዎቹ የሚወስዷቸው ሰዎች አልተመለሱም፡፡

ከነዚህ ክስተቶች ሁለት ሳምንት በኋላም ወደ 43 የሚሆኑ አስከሬኖች በተከዜ ወንዝ ላይ መገኘታቸውን የዜና ወኪሉ በዘገባው አስፍሯል፡፡

በተከዜ ወንዝ ላይ ተገኝተዋል የተባሉ አስከሬኖችን በተመለከተ ሌላ ዘገባ ያስነበበው ሴኤንኤን በበኩሉ፣ የአስከሬኖቹ ብዛት 60 አካባቢ መሆኑን በፎቶ ግራፍ አስደግፎ ዘገበ ሲሆን፣ አገኘኋቸው ያላቸው የዐይን እማኞችም ከአስከሬኖቹ መካከል እጅና እግራቸው ወደ ኋላ የተጠፈሩ ስለመኖራቸውም አመልክቷል፡፡

ቴሌግራፍ በጉዳዩ ላይ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደርና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን አስተያየት ብጠይቅም ምላሽ አልሰጡኝም ብሏል፡፡

በተመሳሳይ ሌላኛው የዜና ተቋም ቢቢሲ በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ስር በሚገኙት በሑመራ፣ አደባይ፣ እድሪስ፣ ቃፍታ ሑመራ ወረዳና ደጓጉም ቀበሌ በትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ጾታዊ ጥቃት፣ ጅምላ እስራትና የመብት ጥሰቶች እየተፈጸመ ነው ሲል መረጃ አስነብቧል፡፡

ይህ በሐምሌ ወር እንደ አዲስ ጀምሯል በተባለ ጥቃት እንደሆነ በመግለጽ ህይወታቸውን ለመታደግ ተደብቀው እንደሚገኙ ገልፀዋል ነው የተባለው፡፡

ሆኖም የአማራ ክልል የፀጥታና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰማ ጥሩነህ ‹‹በተባሉት አካባቢዎች ችግር ደርሶብኛል ብሎ ወደ ቢሮዬ ሪፖርት ያደረገ አንድም ትግርኛ ተናጋሪ የለም። እኔ በማስተዳድረው አካባቢ የሚኖር ሰው ጥቃት ሳይደርስበት እንዲኖር ማድረግ ደግሞ የእኔ ሥራ ነው›› በማለት የቀረቡትን ክሶች ውድቅ አድርገዋቸዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img