Friday, October 18, 2024
spot_img

“ሸኔ” በምእራብ ወለጋ ዞን የቆንዳላ ወረዳ 10 ሰዎችን ማገቱን የወረዳው አስተዳዳሪ ገለጹ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ነሐሴ 27፣ 2013 ― በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የፈረጀውና በመንግስት “ሸኔ” የሚባለው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በሚል የሚጠራው ቡድን በምእራብ ወለጋ ዞን ቆንዳላ ወረዳ በፈፀመው ጥቃት በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን እንዲሁም አስር ሰዎችን ማገቱን የወረዳው አስተዳዳሪ ገልጸዋል፡፡

ኢዜአ የቆንዳላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ቡላ ደመረን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በወረዳው “ሸኔ” በፈጸመው ጥቃት የንጹሃን የተገደሉ ሲሆን፣ በርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተዘርፈው በእሳት ተቃጥለዋል።

“በጥቃቱ ሸኔ 10 ሰዎችን አግቶ ወስዷል” ያሉት አቶ ቡላ ደመረ፤ 24 ንጹሃን ዜጎችን መግደሉንም ነው ያመለከቱት፡፡

ቡድኑ የወረዳውን ፍርድ ቤት እና የአቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ሙሉ በሙሉ በእሳት ከማጋየቱ በተጨማሪ፣ 4 የመንግስት አመራሮች መኖሪያ ቤቶችንም አቃጥሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቆንዳላ ቅርንጫፍን አንዲሁም በ34 የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና ተቋማት ላይ ዝርፊያ መፈጸሙን ያስታወቁት የወረዳው አስተዳዳሪ፤ በወረዳው የሚገኝ የ2ኛ ደረጃ ትምህት ቤት ንብረት እና የተማሪዎችን ማስረጃ ማውደሙንም ተናግረዋል።

የ“ሸኔ” ታጣቂዎች በአጠቃላይ በወረዳው ከነሃሴ 9 ጀምሮ በፈጸሙት ጥቃት ከ200 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የቆንዳላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ቡላ ደመረ ገልጸዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img