አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ነሐሴ 27፣ 2013 ― የአሜሪካው የዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስአይዲ) አስተዳዳሪ ሰማንታ ፓወር ከወራት በፊት የአውሮፓ ኅብረትን ወክለው ኢትዮጵያ ተገኝተው ከነበሩት የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሀቪስቶ ጋር በኢትዮጵያ ጉዳይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ስላለው የሰብአዊ አቅርቦት ሁኔታ እንዲሁም በቀጣይ የኢትዮጵያውያንን ሰቆቃ ለመግታት በቅንጅት የመስራት አስፈላጊነት ላይ መምከራቸውን ሰማንታ ፓወር የሚመሩት ዩኤስአይዲ አስታውቋል፡፡
አስተዳደሪዋ በውይይቱ ወቅት በቅርቡ በኢትዮጵያ ስለነበራቸው ጉብኝት አንስተው የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል እርዳታ እንዳይደርስ ጋርጧል ያሉትን ቢሮክራሲያዊ እንቅፋት እንዲያነሳ በጋራ ጫና ማሳደር እንዳለባቸው ገልጸዋል ነው የተባለው፡፡
ሁለቱ ግለሰቦች በውይይታቸው ሕወሓት በአፋር እና አማራ ክልሎች ጥቃት መፈጸሙ በሰብአዊ አቅርቦቱ ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ አስመልክቶም የተነጋገሩ ሲሆን፣ ሰማናታ በዚሁ ወቅት የሚመሩት ድርጅት ከአካባቢዎቹ ለተፈናቀሉ እርዳታ እያደረሰ እንደሚገኝም መግለጻቸውን ድርጅታቸው አክሎ ገልጧል፡፡