Wednesday, November 27, 2024
spot_img

የሲቪል ማኅበራትን በተመለከተ እየወጡ የሚገኙ መመሪያዎች ስጋት መፍጠራቸው ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ነሐሴ 27፣ 2013 ― በ1997 የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ የወቅቱ መንግሥት ኢሕአዴግ፣ በሕግ ብሎም በአስተዳደራዊ ጫናዎች አዳክሞት ቆይቷል የሚባለው የሲቪል ማኅበራት እንቅስቃሴ ባለፈው ሁለት ዓመት መሻሻል ማሳየቱ በርካቶች ይናገራሉ።

ለዚህም መሠረታዊ ተብለው ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል ከሁለት ዓመታት በፊት የተሻሻለው የሲቪል ማኅበራትን የሚያስተዳድረው ሕግ ይገኝበታል።

ታዲያ እነዚህን መሻሻሎች እንዳይቀለብሱ ያሰጉ አዳዲስ መመሪያዎች እየወጡ መሆኑን ተከትሎ በሲቪል ማኅበረሰቡ ዘንድ ቁጣን ብሎም ስጋት መፍጠሩ እየተነገረ ይገኛል፡፡

አዋጁን ለማስፈጸም ይጸድቃሉ ተብለው የሚጠበቁት አጠቃላይ መመሪያዎች ቁጥር 17 ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ አራቱ ከሁለት ሳምንት በፊት ጸድቀዋል።

እነዚህ አወዛጋቢ መመሪያዎች የእናት ሕጉን መንፈስ፣ ዓላማ ብሎም ግልጽ ድንጋጌዎችን የሚቃረኑ እንዲሁም የመጽደቅ ሂደታቸውም ሕግን ያልተከተለ በሚል ትችት እየቀረበባቸው እንደሚገኝ የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡

የዜና ተቋሙ በረቂቅ ደረጃ ካሉት መመሪያዎች መካከል በሁለቱ ላይ አይሲኤንኤል የተሰኘ ዓለም አቀፍ በሲቪል ማኅበራት ጉዳይ ላይ የሚሰራ ተቋም ያዘጋጀውን ትንተና ዋቢ ያደረገው ዘገባው የመንግሥት ቁጥጥር በተመለከተ ማኅበራቱን ለመቆጣጠር የወጣው መመሪያ ዓላማ ተብለው ከተቀመጡት ነጥቦች መካከል “የድርጅቶቹ አሰራር ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለበት እንዲሁም ለኅብረተሰቡ የላቀ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን ማረጋገጥ” የሚለው አንዱ መሆኑነ ገልጧል፡፡

በዚህ ድንጋጌ ላይ በተለይም “የላቀ ጥቅም” ለትርጉም የተጋለጠ ለሲቪል ማኅበራቱ እንዲሁም ለኤጀንሲው ለክትትል እንዲሁም ለልኬት የሚያስቸግር አገላለጽ መሆኑን ሰነዱ ያሰረዳል።

እንዲሁም ሕጎች ግልጽ በሆነ ቋንቋ መጻፍ እንዳለባቸው የሚደነግጉ ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን ከግምት ያላስገባ ነው ሲልም ይተቻል።

“ኤጀንሲው ድርጅቶች ሥራቸውን በሕግ መሠረት ማከናወናቸውን ለማረጋገጥ አስፈላጊ ሆኖ ባገኘው በማናቸውም መንገድ በመደበኛነት ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይችላል” ሲል የቁጥጥር መመሪያው በአንቀጽ 6 ስር ይደነግጋል።

በተለይም “በማናቸውም መንገድ” የሚለው ሐረግ ለኤጀንሲው እጅግ የተለጠጠ እና ለትርጉም ክፍት የሆነ ስልጣን የሚሰጥ እና ለሕገወጥ አካሄዶች በር ከፋች ነው ሲል ሰነዱ ያትታል።
እንዲሁም ለክትትልና ቁጥጥር ዓላማ ሲባል ኤጀንሲው የተለያዩ መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ የቁጥጥር እና የክትትል እቅድ እንደሚያወጣ ይደነግጋል።

ከ3 ሺህ 500 በላይ የሲቪል ማኅበራትን ለሚቆጣጠረው ለኤጀንሲው ይህ አዲስ አሰራር ጫና የሚፈጥር ነው ሲልም ይኸው በአይሲኤንኤል የተዘጋጀው ሰነድ ያስረዳል ነው የተባለው።

እነዚህ መመሪያዎች ላይ አስተያየት የሰጡ የሕግ ባለሞያ መመሪያው ክልከላ የሚመስሉ እና ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጣቸውን በመጥቀስ፣ አንዳንዶቹ ከአዋጁ ጋር እስከመቃረን የሚደርሱ እንደሆነ እና ይህም አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሲቪል ማህበራት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላው በበኩላቸው ኤጀንሲው መመሪያዎቹ ከመጽደቃቸው በፊት የተለያዩ ውይይቶችን እያካሄደ እንደሚገኝ እና የቀረቡ ቅሬታዎችንም እንደሚያስተናግድ ተናግረዋል።

እስካሁን ድረስ አራት መመሪያዎች የጸደቁ ሲሆን አንድ መመሪያ ቦርዱ እንዲያጸድቀው መቅረቡንም ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም አምስት መመሪያዎች በውይይት ላይ ሲሆኑ፣ ሌሎች ስምንት መመሪያዎች በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም አክለዋል።

አቶ ፋሲካው አክለውም ከሃምሳ የሚበልጡ የሲቪል ማኅበራት ጥምረቶችን በመሰብሰብ ረቂቆቹን እንዲመለከቱ ብሎም አስተያየታቸውን ሙሉ ይሰበሰባል። እንዲሁም በእያንዳንዱ መድረክ የሚነሱ ሃሳቦች እንደሚመዘገቡ እና ሁሉንም ለማሻሻል እንደሚሞክሩም ተናግረዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img