አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ነሐሴ 25፣ 2013 ― ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚሰጠው ሂጅራ ባንክ የፊታችን ቅዳሜ ነሐሴ 29፣ 2013 የመጀመሪያውን ቅርንጫፉን ክፍት በማድረግ ሥራ እንደሚጀምር አስታውቋል።
በአገሪቱ ታሪክ ሙሉ በሙሉ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት በመስጠት ሁለተኛው የሚሆነው ሂጅራ፣ በዕለቱ የመጀመሪያውን ኦሎምፒያ አካባቢ ነጃሺ የተሰኘ ቅርንጫፉን የሚከፍት ሲሆን፣ በተጨማሪም በዚሁ የመጀመሪያው ሳምንት በተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ እንዲሁም በተለያዩ የክልል ከተሞች 11 ቅርንጫፎች እንደሚከፍትም ገልጿል።
በተያዘው ዓመት ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ በአገሪቱ ታሪክ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት በመስጠት ፈር ቀዳጅ ነው የሚባለው ዘምዘም ባንክ ሥራ መጀመሩ ይታወቃል።
ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ለማቋቋም የሚፈቅደው ሕግ ከመውጣቱ ቀደም ብሎ ባንኮች ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመስኮት ደረጃ እንዲሰጡ ተፈቅዶ የነበረ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረት እስካሁን ወደ 11 ባንኮች አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
ይህ በመስኮት ደረጃ የሚሰጠው አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህ እነዚህ ባንኮች ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ያሰባሰቡት የተቀማጭ ገንዘብ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ከወለድ ነፃ ያሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በ2013 ሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ከ64 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡