Sunday, October 13, 2024
spot_img

የደሴ ከተማ አስተዳደር ለተፈናቃዮች ድጋፍ ለማድረግ መቸገሩን ገለጸ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ነሐሴ 22፣ 2013 ― የደሴ ከተማ አስተዳደር ወደ ከተማው የሚገቡ የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የሰብዓዊ ድጋፎች ለማድረግ ተችግሬያለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡

የደሴ ከተማ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ምሳዬ ከድር እንደገለጹት፣ የቀይ መስቀል፣ የአደጋ መከላከያ እና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት የተለያዩ አካላት ድጋፍ እያደረጉ ቢሆንም፣ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ለመጣው የተፈናቃዮች ቁጥር የተሰጡ የሰብዓዊ ድጋፎች አነስተኛ ናቸው ብለዋል። አያይዘውም በየቀኑ የሚገቡትን ተፈናቃዮች ለማስተናገድ ተከታታይ የሆነ ድጋፍ ያስፈልጋል ሲሉ ነው የገለጹት።

ጉዳዩ በመንግሥት በኩል ለጥቂት ጊዜ ብቻ ትኩረት ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ሰዓት እየተረሳ በመምጣቱ የሚሰጡ ድጋፎች መቀነሳቸውን ጠቅሰዋል። በዚህም ተፈናቃዮችን ለማስተናገድ ከፍተኛ ችግር ገጥሞናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የከተማው ማኅበረሰብ ከሚያደርገው ድጋፍ ውጭ በመንግሥት በኩል ተከታታይ ዕርዳታዎች ባለመምጣታቸው ችግር ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ቀን ድረስ ወደ ከተማዋ የሚገቡ ተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን፣ በቀን እስከ 200 ሰዎች ከተለያዩ አካባቢዎች እየገቡ ነው ብለዋል። በዚህም ከ300 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በአካባቢው እንደሚገኙ ነው የጠቆሙት። ወደ ደሴ ከተማ እየገቡ ያሉ ተፈናቃዮች በሽብርኝነት የተፈረጀው ህወሓት ወረራ ከፈጸመባቸው የሰሜን ወሎ አካባቢዎች እና የአፋር ክልል መሆኑን ምሳዬ ይናገራሉ።

በዚህም የሰሜን ወሎ ዞን አጠቃላይ ነዋሪዎች፣ ከአፋር ክልል የአንድ ወረዳ ነዋሪዎች፣ እንዲሁም የሌሎች አካባቢ ተፈናቃዮች ወደከተማው መግባታቸው ነው የተገለጸው። በደሴ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ሲጠቀሙባቸው የቆዩትን አምስት መጠለያ ጣቢያዎች ባሳለፍነው ሰኞ ወደ ዘጠኝ እንዳሳደጉት የገለጹት የመምሪያ ኃላፊዋ፣ መጠለያዎቹን የማይጠቀሙና ቤት ተከራይተው እንዲሁም ዘመድ ጋር ተጠግተው የሚኖሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

በመጠለያ ለሚገኙት የሕብረተሰብ ክፍሎች የከተማው ነዋሪዎች ምግብ እና አልባሳት በማሟላት የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ ነው የገለጹት። በከተማዋ የሚገኙ የጤና ተቋማት የጤና አገልግሎትን በመስጠት እንዲሁም ገንዘብ ያላቸው ገንዘብ በመስጠት ተፈናቃዮችን እያገዙ ይገኛሉ ተብሏል። የደሴ ከተማ ነዋሪዎች በየሠፈሩ የራሳቸውን አደረጃጀት ፈጥረው አካባቢያቸውን እየጠበቁ እንደሚገኙም ምሳዬ ከድር ተናግረዋል ሲል የዘገበው አዲስ ማለዳ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img