አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ነሐሴ 22፣ 2013 ― የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለቀጣይ ሦስት ወራት በከተማው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መጨመርም ሆነ ተከራይን ከቤት ማስወጣት የሚከለክልውን ደንብ አጽድቋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማው የኑሮ ውድነት እየተባባሰ መምታቱን የገለጸው መስተዳድሩ፣ የኑሮ ውድነቱ በአብዛኛው አሳማኝ እና ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው በሰውሰራሽ ምክንያቶች የተፈጠረ መሆኑንም ገልጧል፡፡ በዚህም የኑሮ ውድነቱ የከተማውን ነዋሪ ለከፍተኛ ችግር እንደዳረገ ነው ያመለከተው፡፡
በከተማው የሚስተዋለውን ችግር ለማጥናትግብረሃይል መቋቋሙን በማስታወስም፣ ግብረ ኃይሉ ከመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ባሻገር አለግባብና የወቅቱን ሁኔታ ያላገናዘበ የቤት ኪራይ ጭማሪ የነዋሪውን ሕይወት በእጅጉ እየፈተነው እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡
ስለሆነም አሁን እየታየ ያለውን አላግባብ የሆነ ነው ያለውን የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ ለመገደብ የነዋሪውን ቅሬታ ምላሽ ለመስጠት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በቀን ማክሰኞ ነሐሴ 18 ባደረገው መደበኛ ስብሰባው የቤት ኪራይ ጭማሪን ለ90 ቀናት ለማገድ በቀረበ ደንብ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ ማጽደቁን ነው ያሳወቀው፡፡
በዚህም መሠረት ደንቡ ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መጨመርም ሆነ ተከራይን ከቤት ማስወጣት ለ90 ቀናት የተከለከለ ሲሆን፣ በቀጣይም ታይቶ ለተጨማሪ ቀናት ክልከላው ሊራዘም ይችላል ተብሏል፡፡
ደንቡን በመተላለፍ ጭማሪ የተደረገበት ተከራይ አቤቱታውን በፅሑፍ ለወረዳው ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት በማቅረብ መፍትሄ እንዲያገኝ የሚቻልበት ሥርዓት በደንቡ የተደነገገ መሆኑ ሲገልጽ፣ በዚሁ መሰረት በሚቀርቡ አቤቱታዎች ላይ ማጣራት ተደርጎ ጭማሪ ባደረገ አካል ላይ በደንቡ ተዘርዝሮ በተቀመጠው መሰረት ተጠያቂ የሚደረግ መሆኑንም የከተማ አስተዳደሩ ጽሕፈት ቤት አሳውቋል፡፡