– አቶ ለማ መገርሳም ከቀድሞ ሥልጣናቸው የተነሱት በመፈንቅለ መንግሥት ነው ብለዋል
አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ነሐሴ 20፣ 2013 ― የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ አመራር አባሉ አቶ ጃዋር መሐመድ የታሰሩት በአማራ ብልጽግና አመራሮች ጥያቄ መሆኑን የኦሮሚያ ብልጽግና የቀድሞ ከፍተኛ አመራር ዶክተር ሚልኬሳ ሚደጋ ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ሚልኬሳ ሚደጋ በቀድሞው ፓርቲያቸው ከታገዱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር ባደረጉት ቆይታ ‹‹የአዴፓ ሰዎች መካከል ጃዋር መሐመድን ካላሰራችሁ ከእናንተ ጋር አንሰራም ሲሉ ነው ኦዴፓ ያሠረው›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ይኸው ጉዳይ ‹‹በስብሰባ ላይ ተጠይቋል›› ያሉት ዶክተር ሚልኬሳ፣ ከአዴፓ 13 ሰዎች ጃዋር ካልታሰረ ‹‹አዴፓን እንለቃለን›› እንዳሉም ነው የገለጹት፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የቀድሞው የኦሮሚያ ብልጽግና አመራር አባሉ በቆይታቸው ስለ ፌዴራሊዝም፣ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዲሁም ስለ ቲም ለማ አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን አስመልክቶ ‹‹የኦሮሞ ህዝብ እኔን ካልደገፈኝ እሰብረዋለሁ ብሎ በግሌ ነግሮኛል›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ፌዴራሊዝምን በተመለከተም እርሳቸው የፖለቲካል ሳይንስ ባለሞያ መሆናቸውን እንዲሁም ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪያቸውንም ጭምር በፌዴራሊዝም ዙሪያ መሥራቸውን በመጠቆም ‹‹የአሁኑ ስርዓት በፊት የነበረውን ያህል የውሸት ፌዴራሊዝም ነው እንኳን ለማለት አያስችልም›› ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ከኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ሲታገዱ ባንድነት አብረዋቸው የነበሩት የቀድሞው የፓርቲ አጋራቸውን አቶ ለማ መገርሳን በሚመለከትም የተናገሩት ዶክተር ሚደቅሳ፣ ከስልጣናቸው የተነሱት ከማእከላዊ ኮሚቴ እውቅና ውጪ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ በአቶ ለማ ላይ የተደረገውን ነገር ‹‹መፈንቅለ መንግሥት›› ነው ብለውታል፡፡
ከዚያ ቀን በኋላ ‹ቲም ለማ› የሚባለው ስብስብ መፍረሱን ያመለከቱት የቀድሞው የኦሮሚያ ብልጽግና አመራር፣ የአቶ ለማን ጉዳይ በተመለከተ በማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ቢጠይቁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ‹‹ሁሉንም ነገር አትፈላፈሉ የሚል መልስ ሰጡኝ›› ብለዋል፡፡
ዶክተር ሚደቅሳ ሚደጋ ከኦሮሚያ ብልጽግና ከታገዱ በኋላ ሥራ ለማግኘት እንደተቸገሩ የተናገሩ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርርሲቲን ጨምሮ ሊቀጥሯቸው ፍላጎት ያሳዩ ሁሉ ‹‹መንግስትን በመስጋት›› ቅጥሩን እንደተዉት ነው የገለጹት፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ ባገኙት የትምህርት እድል ወደ አሜሪካን ማቅናታቸውንም ተናግረዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ጽሕፈት ቤት በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትርና የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ለማ መገርሳ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ የሆኑት ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን እና ቀደም ሲል በኦሮሚያ ክልል የመሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ በኋላም የብልጽግና ፓርቲ ኦሮሚያ ቅርንጫፍ አማካሪ ዶክተር ሚልኬሳ ሚደጋ መታገዳቸውን ያሳወቀው አምና በዚህ ወቅት ነበር፡፡
(የዶክተር ሚልኬሳ ሚደጋን ሙሉ ቃለ ምልልስ የአማርኛ ትርጉም ከጥቂት ቆይታ በኋላ በአምባ ዲጂታል የሚለቀቅ ይሆናል)