Thursday, November 28, 2024
spot_img

በአሸባሪነት ከተፈረጀው ሕወሓት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ ከ1 ሺሕ 600 በላይ ሰዎችን መያዙን ፖሊስ አሳወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ነሐሴ 19፣ 2013 ― መንግሥት አሸባሪ ብሎ ከፈረጀው ሕወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 1ሺሕ 642 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግሥቴ እንደገለጹት፣ ከሕወሓት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ ሰዎችን በማደን በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ እየተደረጉ ናቸው፡፡

እስካሁን ድረስ በተካሄደው የተቀናጀ ምርመራ ከሕወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ 1 ሺ 642 ሰዎች፣ በተለያዩ አካባቢዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ አስታውቀዋል።

ከተጠረጠሩት ሰዎች በተጨማሪ ለሕወሓት ቡድን ሕገ ወጥ ተልዕኮ መጠቀሚያ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ የንግድ ድርጅቶች ተዘግተው ምርምራ በመካሄድ ላይ እንደሆነ ገልጸዋል።

ለሕወሓት ቡድን መጠቀሚያ የነበሩ ሆቴሎች፣ ሕንፃዎች፣ መጋዘኖች፣ የኢንቨስትመንት እርሻዎች፣ ፋብሪካዎችና ሪል ስቴቶችን ጨምሮ 1 ሺሕ 616 ያህል የንግድ ድርጅቶች እንዲዘጉ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ፖሊስ ባከናወነው ሥራ 58 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን፣ በተጨማሪም 93 የባንክ ሒሳቦች እንዳይንቀሳቀሱ በማሳገድ የባንክ ሒሳቦቹ ምን ያህል ገንዘብ እንደያዙ በማጣራት ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።

በቀጣይም ከሕወሓት ጋር ግንኙነት ያላቸውንና ተልዕኮ ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ አካላትን ለማደን የተቀናጀ የምርመራ ሥራና ክትትል የሚደረግ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ለዚህም ተግባር አገር አቀፍ የሆነ የፖሊስ ምርመራ የጋራ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም መደረጉን ተናግረዋል።

ግብረ ኃይሉ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚመራ እንደሆነ፣ ሁሉንም ክልሎች ከሌሎች አጎራባች ክልሎች ከሚገኙ የወንጀል ምርመራ ዘርፎች ጋር በአንድ ያጣመረ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ግብረ ኃይሉ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እንደሚመራና በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሕወሓት ያሰማራቸውን ሽብርተኞች በመያዝ ለሕግ ከማቅረብ ባሻገር፣ በተደራጁ ወንጀሎችና በሌሎች የሕግ ጥሰቶች ላይ የሚሳተፉ አካላትን በመቆጣጠር የሕግ የበላይነት የሰፈነባትን አገር ለማስቀጠል ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img