አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ነሐሴ 19፣ 2013 ― የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትን ለማደናቀፍ በ37 ሺሕ ኮምፒውተሮች ላይ ተነጣጥሮ የነበረ የሳይበር ጥቃትን ቀድሞ ማከሸፍ መቻሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው አስታውቀዋል፡፡
ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰው፤ በግድቡ ላይ የተለያዩ ሀገራት የተለያዩ ፍላጎት ስላላቸው በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ሙከራዎችን ያደረጉ ነበር ብለዋል።
ከዚህም ውስጥ ሌሎች ተቋማትን ኢላማ አድርጎ የህዳሴ ግድብን 2ኛ ዙር ውሃ እንዳይሞላ ሲደረግ የነበረ ሙከራን ለአብነት አንስተዋል።
በተለይም ሳይበር ሆረስ ግሩፕ በ2012 የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት ላይ እንዲሁም በ2013 ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ወቅት በኢትዮጵያ ውስት የሚገኙ ኮምፒውተሮችን በመለየት ጥቃት ለማድረስ ሙከራዎችን ሲያደርግ እንደነበረ ጠቅሰዋል፡፡
ይህ ቡድን በኢትዮጵያ ሲስተም ውስጥ የነበሩ ከ37 ሺህ በላይ ኮምፒውተሮችን ለማጥቃት ተዘጋጅቶ እንደነበረ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የኢንተለጀንስ ቡድን ቀድሞ ማስጣሉንም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ለሌሎች የሜጋ ፕሮጀክቶቿ ልዩ ትከረት በመስጠት ክትትል እና ቁጥጥር እንደምታደርግም ዶክተር ሹመቴ አክለው ማስታወቃቸውን የዘገበው አል ዐይን ሚዲያ ነው፡፡