አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ነሐሴ 16፣ 2013 ― በቅርቡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለቤቱ የተበደረውን እዳ ባለመክፈሉ ሐራጅ የወጣበትን የተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ዋና መስሪያ ቤትን ለመግዛት አያት ሪል ስቴት 615 ሚሊዮን ብር ማቅረቡ ተሰምቷል፡፡
ባለፈው ሐሙስ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛጉዌ ቅርንጫፍ በተከናወነው ጨረታ ከአያት ሪል ስቴት በተጨማሪ ኮሜርሻል ኖሚኒስ 600 ሚሊዮን ብር ማቅረቡን የፎርቹን ዘገባ ያመለክታል፡፡
የተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ዋና መስሪያ ቤት በሲኤምሲ አካባቢ 13 ሺሕ 203 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ከፀሓይ ሪል ስቴት ቅንጡ መኖሪያ ቤቶች 200 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡
ንብረቱ ለሐራጅ የወጣው የድርጅቱ ባለቤቶች ዕዳቸው ባለመክፈላቸው መሆኑ ቢነገርም፣ እዳቸው ምን ያህል እንደሆነ ባንኩ የደንበኛውን ምሥጢር ለመጠበቅ በሚል ይፋ አለማድረጉን በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ባለፉት ዓመታት በኮንስትራክሽን ዘርፉ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ሥሙ ይጠራ የነበረው ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ከሳምንታት በፊት ሌላኛው ብብዙ የሚታወቅበት ንብረቱ ኤድና ሞል በተመሳሳይ ሐራጅ እንደወጣበት ይታወቃል፡፡
በወቅቱ ኤድና ሞልን ለመግዛት በወጣው ጨረታ የቻይናዊያን ንብረት የሆነው ኢስት ስቲል ከፍተኛ የተባለውን 810 ሚሊዮን ብር ማቅረቡ መነገሩ የሚታወስ ነው፡፡