Sunday, September 22, 2024
spot_img

በተለያዩ ሃገራት የተከፈቱ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ብዙዎቹ እየታጠፉ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ነሐሴ 13፣ 2013 ― በተለያዩ ሃገራት ከተከፈቱ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች አብዛኞቹ እየታጠፉ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጽህፈት ቤቶቹ ታጥፈው ወደ ዋናው ኤምባሲው የሚሄዱበት አሰራር እየተከተልን ነው ብሏል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ጉዳይ በተመለከተ ዛሬ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያው ሃገራዊ ለውጡን ተከትሎ ልክ እንደ መከላከያ እና ብሔራዊ ደህንነት ሁሉ የውጭ ጉዳይ ሪፎርም ተጠናቋል ያሉት ቃል አቀባዩ “ብቁና ትክክለኛ ቁመና ያለው” የኤምባሲና የቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን ለማቋቋም በማሰብ አብዛኞቹ መታጠፋቸውን ገልጸዋል።

እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ “አንዳንዶቹ “ነገሮች በወጉ ሳይጠኑ በግምት የተከፈቱና ለመዝጋት የከበዱ፤ ከሚገባውም በላይ የሰው ኃይል የያዙ ናቸው”።

በመሆኑም የሰው እና የምጣኔ ሃብት አቅምን በወጉ ለመጠቀም በማሰብ አብዛኞቹ የኤምባሲና የቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እየተዘጉ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ለዚህም በቻይና እና አሜሪካ ያሉ ሶስት ሶስት ጽህፈት ቤቶችን በማሳያነት አንስተዋል። እነዚህን ዘግቶ ወደ ዋና ከተሞቹ ወደ ቤጂንግ እና ዋሽንግተን የማምጣት ጉዳይ እንደሆነም ነው የገለጹት።

“አሜሪካን ሃገር ሎስአንጀለስ እና ሚኒያፖሊስ ቆንስላዎች አሉ አያስፈልጉም ዋሽንግተን መሆን ይችላሉ” ነው፤ ይህ በሌሎች ሃገራት የተለመደ እንደሆነ ነው አምባሳደሩ የተናገሩት።

ርምጃው አምባሳደሮች ወደሃገራቸው ተመልሰው በብር እየተከፈላቸው አስፈላጊ ሲሆን እየተመላለሱ ጥቂት የስታፍ አባላትንና ባለሙያዎችን ይዘው የሚሰሩበትን ሁኔታ ታሳቢ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

በእንዲህ ዐይነት ሁኔታ በዲጂታል ታግዘው በብቃት የሚሰሩ ኤምባሲዎች እንዳሉ ከግምት ገብቷልም ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ከሃገራት ጋር ንግግር ተደርጎ በርካታ ጽህፈት ቤቶች ታጥፈው ወደ ዋናው ኤምባሲው የሚሄዱበት አሰራር እየተከተልን እንገኛለንም ብለዋል፡፡

“ኢትዮጵያ ‘ኤምባሲዎችን ዘጋች’ የሚለው የተጋነነ ነው” የሚሉት አምባሳደር ዲና፣ ብዙዎቹ የጽህፈት ቤቶቹ ሰራተኞች በቅርቡ ወደ ሃገር ቤት እንደሚመጡና መደበኛ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን እንደሚወስዱ አስታውቀዋል መባሉን የዘገበው አል ዐይን ነው።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img