Sunday, October 6, 2024
spot_img

የቻይናው ኤክዚም ባንክ ለኢትዮጵያ በብድር ሊለቅ የነበረውን 339 ሚሊዮን ዶላር ከመስጠት ታቀበ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ነሐሴ 12፣ 2013 ― የቻይናው ኤክዚም ባንክ ለኢትዮጵያ ሊሰጥ የነበረውን የብድር ገንዘብ ከመስጠት መታቀቡን በገንዘብ ሚኒስትር አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ነግሬውኛል ብሎ ሬውተርስ አስነብቧል።

የዜና ወኪሉ የቻይናው ኤክዚም ባንክ ለኢትዮጵያ ከመስጠት የታቀበው የብድር መጠን 339 ሚሊዮን ዶላር ነው ያለ ሲሆን፣ በስልክ ነግረውኛል ያለው ደግሞ የገንዘብ ሚኒስቴር የቻይና ትብብር ዳይሬክተር ደምሱ ለማ ናቸው።

ነገር ግን የቻይናው ኤክዚም ባንክ ለኢትዮጵያ ብድር ለመልቀቅ በማቅማማት ላይ ያለ ብቸኛው የፋይናንስ ተቋም አይደለም ተብሏል።

ሰኔ ወር ላይ በገንዘብ ሚኒስቴር የታተመ አንድ ሰነድ እንዳመለከተው የውጭ አበዳሪዎች አስከ መጋቢት መጨረሻ ድረስ 11 ቢሊዮን ዶላር ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቅ እንደነበር የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል።

የዓለም ባንክ አንድ አካል የሆነው የዓለም አቀፉ የልማት ትብብር ማኅበር (ኢንተርናሽናል ዴቨሎፕመንት አሶሲየሽን) 3.3 ቢሊዮን ዶላር ይለቃል ተብሎ ይጠበቅ የነበረ ሲሆን ይህን እስከአሁን ተግባራዊ አላደረገም።

ሚኒስቴሩ በሰነዱ ከጠቀሳቸው ሌሎች አበዳሪ ተቋሟት አንዱ ግዙፉ የዓለም የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ሲሆን፣ ተቋሙ 2.7 ቢሊዮን ዶላር እስከ አሁን ለኢትዮጵያ አልለቀቀም።

ከውጭ አበዳሪዎች ትልቅ የምትባለው ቻይና 1.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር አልለቀቀችም። ከላይ ከተጠቀሱት አበዳሪዎች ሌላ የአፍሪካ ልማት ባንክ እና ሌሎች የንግድ ባንኮች ይገኙበታል።

ይህ የውጭ አበዳሪዎች ተጨማሪ ብድር ለኢትዮጵያ ለመልቀቅ አለመፍቀዳቸው አገሪቱ ላይ እየተካሄዱ ያሉ መጠነ ሰፊ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ሊያስተጓጉል እንደሚችል ይገመታል መባሉም በዘገባው ተጠቅሷል።

በውጭ ብድር ተጠቃሚ እየሆኑ ከቆዩት ፕሮጀክቶች መካከል እርሻ፣ ትራንስፖርት፣ ኮሚዩኒኬሽን፣ አውራ ጎዳናዎች እና የባቡር ፕሮጀክቶች ይገኙበታል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img