Wednesday, October 16, 2024
spot_img

ባንኮች ለሠራዊቱ እንዲያዋጡ በተጠየቁት ግማሽ ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ገንዘብ ግራ መጋባቸው ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ነሐሴ 12፣ 2013 ― በአገር ውስጥ የሚገኙ ባንኮች ለአገር መከላከያ ሠራዊት እና ለክልል ልዩ ኃይሎች እንዲያዋጡ በተጠየቁት 400 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ግራ መጋባቸው ተሰምቷል።

ግራ መጋባት ውስጥ ወድቀዋል የተባሉት 18 ባንኮች በማኅበራቸው በኩል ድጋፉን እንዲያደርጉ ቀድሞ ጥያቄ አቅርበውላቸዋል ለተባሉት ለአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር፣ ለመከላከያ ሠራዊት እና ለአማራ ክልላዊ መንግስት በጻፉት ደብዳቤ ለፌዴራል ሠራዊት እና ለክልል ኃይሎች ምን ያህል ድርሻ መስጠት እንደሚኖርባቸው ማብራሪያ መጠየቃቸውን የፎርቹን ዘገባ ያመለክታል።

በማኅበሩ ሊቀመንበር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንቱ አቤ ሳኖ በኩል በተጻፈው ደብዳቤ ባንኮቹ ከድርሻው በተጨማሪ ገቢ የሚያደርጉት የት እንደሆነም ነው የጠየቁት።

እነዚህ ባንኮች የት እንደሚያስገቡ እና ድርሻውን በተመለከተ ማብራሪያ እየጠበቁ ቢሆንም፣ አሁን ለተጠየቁት የገንዘብ ድጋፍ ካልተጣራ ትርፋቸው ለማዋጣት መስማማታቸውን የእናት ባንክ ፕሬዝዳንት ኤርሚያስ አንዳርጌ መናገራቸው ተመላክቷል።

አሁን ወደ ግማሽ ቢሊዮን ብር ድጋፍ የተጠየቁት ባንኮቹ በተያዘው ዓመት አጋማሽ ግድም ለመከላከያ ሠራዊት እና በጦርነት ለተፈናቀሉ መልሶ ማቋቋሚያ ወደ ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ዘገባው አስታውሷል።

ከባንኮቹ በተጨማሪ የመድኅን ድርጅቶች እና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ደግሞ ወደ አንድ መቶ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img