አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ነሐሴ 12፣ 2013 ― የአሁኑን የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን ዳግም መመረጥ የሚቃወመው ድርጅት ለዓለም ጤና ድርጅት አለቃነት የሚደረገው ምርጫ በግልጽ እንዲካሄድ መጠየቁ ተሰምቷል፡፡
ኤድስ ሔልዝኬር ፋውንዴሽን (ኤኤችኤፍ) የተባለው ይኸው ድርጅት የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት የሚወዳደሩ ዕጩዎችን በአንድ ወር ውስጥ ማቅረብ እንደሚጀምሩ አስታውሶ፤ ምርጫው ግልጽነት ሊኖረው ይገባል ብሏል።
‹‹የኮሮና ወረርሽኝን በግልጽ መቆጣጠር ያልቻሉትን ዶ/ር ቴድሮስን ማን ይተካቸዋል ነው ጥያቄው›› ያሉት የድርጅቱ ፕሬዝዳንት ማይክል ዌኒስቲን፣ ‹‹ምርጫው ግልጽ መሆን አለበት›› ሲሉ መናገራቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡
የዓለማችን ግዙፉ በኤድስ ጉዳይ የሚሰራው ኤድስ ሔልዝኬር ፋውንዴሽን (ኤኤችኤፍ) በሰኔ ወር አጋማሽ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለሁለተኛ ዙር የዓለም ጤና ድርጅትን በዋና ዳይሬክተር ማዕረግ ለአምስት ዓመታት ዳግም ለመምራት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን በማስታወስ፣ ዶ/ር ቴድሮስ በቀጣይ የዓለም ጤና ድርጅትን ለመምራት ዳግም መመረጥ የለባቸውም ያላቸውን ምክንያቶች ዘርዝሮ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ለረዥም ዓመታት የኢትዮጵያ ጤና ሚሚንስትር እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሆነው ያገለገሉት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ተብለው የተሾሙት በ2009 ነበር፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ድርጅቱን ለቀጣይ አምስት ዓመት የሚመሩ እጩዎችን የፊታችን መስከረም ወር አጋማሽ ላይ ይለያል ተብሎ ተጠብቋል፡፡
ድርጅቱ ለቀጣይ አምስት ዓመታት በአለቃነት የሚመራውን ግለሰብ በሚቀጥለው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ይፋ የሚያደርግ ይሆናል።