አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ነሐሴ 12፣ 2013 ― የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ጄፋሪ ፊልትማን ጋር መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በፌስቡክ ገፁ አሳውቋል፡፡
አቶ ደመቀ ‹‹ወራሪ ሀይል›› ሲሉ የጠሩት ሕወሃት በሰሜን አዝ ላይ ከፈጸመው ጥቃት ጀምሮ አሁን ያለበትን ዝርዝር ሁኔታን አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ይህ ኃይል በአማራና አፋር ክልል ግልፅ ወረራ፣ ዘረፋ፣ ግድያና ማንኛውንም ሰብአዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥፋቶችን እያካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን ሁሉ ጥፋትና የሀገር ክደት እየፈፀመ የአሜሪካ መንግስት ድርጊቱን በሚመጥን ደረጃ እንዲሁም የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት የሚመጥን ጥፋቱን የሚያጋልጥ ምላሽ መስጠት እንደሚገባና ም/ጠ/ሚኒስትሩ ገንቢ ሚና እንደሚጠብቁ መግለፃቸው በመረጃው ሠፍሯል፡፡
አምባሳደር ጄፋሪ ፊልትማን በበኩላቸው የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያ ህዝብ በሕወሃት ላይ ያለውን አመለካከት በውል እንደሚረዱ ገልጸዋል የተባለ ሲሆን፣ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላት ፖሊሲ መሠረቶች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ሠላም እና አንድነት በማስጠበቁ፣ በማረጋገጡ እና በማስቀጠሉ ላይ የተመረኮዘ መሆኑንና የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በነዚሁ መሠረታዊ መልህቆች ላይ ተመስርቶ እንደሚቀጥል ገልፀዋል። አክለውም በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ቀጠናዊ ትርጉም እንዳለው መግለፃቸው በመረጃው ተካቷል፡፡
በመጨረሻም አምባሳደር ጄፋሪ ፊልትማን በአገራችን በሚኖራቸው ቆይታ ከተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ተብሏል።