Wednesday, October 16, 2024
spot_img

መንግሥት ሁሉን አቀፍ «ብሔራዊ የሀገር ሉዓላዊነት እና የሕዝብ ደህንነት ማስከበሪያ ዘመቻ ግብረ ኃይል» እንዲያቋቁም ኢዜማ ጥሪ አቀረበ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ነሐሴ 10፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) መንግሥት ሁሉን አቀፍ «ብሔራዊ የሀገር ሉዓላዊነት እና የሕዝብ ደህንነት ማስከበሪያ ዘመቻ ግብረ ኃይል» እንዲያቋቁም ኢዜማ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ፓርቲው ‹‹የአማፂያንን የጦር አውርድ ለመግታት ዜጎች በጋራ መቆም ይኖርብናል›› የሚል ርእስ በሰጠው መግለጫው፣ ‹‹ሕወሃት አሁን ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለው እና አደጋ የደቀነው በአማራ እና በአፋር ክልሎች ቢሆንም ይህን ጉዳት እና አደጋ አሁን በአስቸኳይ ማቆም ካልቻልን ሳይውል ሳያድር በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች መከሰቱ የማይቀር ነው›› ብሏል።

ይህንኑ ተጋርጧል ያለውን አደጋ ‹‹በብቃት ለመመከት እና ለማስቀረት›› ሁሉንም በአንድነት አሰባስቦ ማሰለፍ የሚችለው የፌደራል መንግሥት በመሆኑ፣ መንግሥት ይህን ግዴታውን ከምንግዜውም በላይ በከፍተኛ ውጤታማነት መወጣት እንዲችል ‹‹የወታደራዊ፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ የፕሮፖጋንዳ፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ እና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ማገዝ እንዲሁም የሀብት ማሰባሰብ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መሠራት ያለባቸው ሥራዎችን ስትራቴጂ እየነደፈ እንዲፈፀሙ ውሳኔ የሚያስተላልፍ «ብሔራዊ የሀገር ሉዓላዊነት እና የሕዝብ ደህንነት ማሰከበር ዘመቻ ግብረ ኃይል» ከመንግሥት መዋቅር ውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ጭምር በማሳተፍ በአስቸኳይ እንዲያቋቁም እና ወደ ሥራ እንዲገባ ጠይቋል፡፡

ይህ የዘመቻ ግብረ ኃይል በዋነኛነት በፌደራል መንግሥት የሚመራ ሆኖ በሁሉም የመንግሥት እርከኖች በተዋረድ የሚደራጅ እና ከላይ የተጠቀሱ ዘመቻው ጋር በተያያዘ ያሉ ሥራዎችን ብቻ የሚያስተባብር ሆኖ እንዲዋቀር የጠየቀው ኢዜማ፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የተለያዩ አደረጃጀቶች ሕወሃትን ከዚህ እኩይ ተግባር ለመግታት እና ለሀገር ሉዓላዊነት እና ለሕዝብ ደህንነት ስጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያደርጉ በማለት ጥሪ አቅርቧል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img