አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ነሐሴ 10፣ 2013 ― የአማራ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ ባሕር ዳር እና ሌላኛዋ የክልሉ ከተማ ጎንደር በትግራይ እና በአማራ ክልሎች እየተደረገ ካለው ውጊያ ጋር ተያይዞ የሰዓት እላፊ ያወጁ የክልሉን ከተሞች ተቀላቅለዋል፡፡
ከነዚህ ሁለት ከተሞች በተጨማሪ ባለፉት ሁለት ቀናት የሰዓት እላፊ ካወጁት መካከል የደብረማርቆስ፣ የደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች ይገኙባቸዋል።
የከተማ አስተዳደሮቹ እነዚህን የእንቅስቃሴ ገደቦች በማያከብሩ ግሰለቦችም ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
በባህር ዳር ከተማ እና አካባቢዋ ስምሪት ከተሰጠው የፀጥታ ኃይሎች ውጭ ህዝቡ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚችለው ከጥዋቱ 12 እስከ ምሽቱ 2 ሰአት ብቻ ነው።
ከነሐሴ 8፣ 2013 ጀምሮ ከምሽቱ 2 ሰዓት በኋላም የእንቅስቃሴ ገደብ መቀመጡንም የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት ማሳወቁን በአስተዳደሩ የማህበራዊ ትስስር ገጽ በኩል ተነቧል፡፡
ድንገተኛ የጤና እና ሌላ አሰቸኳይ ጉዳይ ሲያጋጥም በአካባቢው ያለውን የፀጥታ አካል በማሳወቅ ብቻ መንቀሳቀስ እንደደሚገባና ከዚህ ውጪ ያለማንም ፈቃድ ህጉን ተላልፎ ሲንቀሳቀስ የተገኘ አካል እርምጃ እንደሚወሰድበት የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በከተማዋ ውስጥ ያሉ መጠጥ ቤቶች፣ ፑል ቤቶች፣ ጭፈራ ቤቶችና ሌሎችም የንግድ እንቅስቃሴዎች ከላይ ከተጠቀሰው ሰዓት ውጪ አገልግሎት እንዳይሰጡ በአዋጁ መከልከሉን ዶ/ር ድረስ ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል ተጀምሮ በቅርብ ቀናት የሕወሓት ኃይሎች ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች በመግፋታቸው የተስፋፋው ጦርነት አሁንም መቀጠሉን በየእለቱ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡