Monday, October 14, 2024
spot_img

ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ 74 ክሶች ፍርድ ቤት መቅረባቸው ይፋ ተደረገ።

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ነሐሴ 9፣ 2013 ― ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ዕለትና በድኅረ ምርጫ በተፈጠሩ ችግሮች በሦስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች 74 ክሶች ቀርበው ውሳኔ ማግኘታቸውን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዓርብ ነሐሴ 7፣ 2013 ይፋ አደረገ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ እንደገለጹት፣ ከስድስተኛው አገራዊ የምርጫ ሒደት ጋር ተያይዞ ለሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ፍርድ ቤት ለሚቀርቡ ጉዳዮች፣ አፋጣኝ ውሳኔ ለመስጠት በየደረጃው 24 ልዩ ችሎቶች ተደራጅተዋል። ለዳኞችም ሥልጠና ተሰጥቶ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተከናውኗል፡፡

የምርጫ ሒደቱ በይፋ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት 21፣ በከፍተኛ ፍርድ ቤት 24 እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት 29፣ በአጠቃላይ ከምርጫ ጋር የተያያዙ 74 ጉዳዮች (ክሶች) ለፍርድ ቤት ቀርበው በነፃነትና በገለልተኝነት የዳኝነት ውሳኔ እንደተሰጠባቸው ተናግረዋል፡፡ ጉዳዮቹ 22 የወንጀል፣ 52 ደግሞ የፍትሐ ብሔር መሆናቸውን አክለዋል፡፡

ክሶቹ ወይም ጉዳዮቹ የቀረቡት 57 በቅድመ ምርጫ፣ አራት በምርጫው ዕለትና ቀሪዎቹ 13 ጉዳዮች በድኅረ ምርጫ የቀረቡ መሆናቸውን ወ/ሮ መዓዛ ጠቁመዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ እንዳብራሩት የወንጀል ጉዳይ ሆነው ወደ ፍርድ ቤት የቀረቡት ክሶች የዕጩ ፖስተር መቅደድ፣ የምርጫ ማስታወቂያን መቅደድ (ማጥፋት)፣ ለማጭበርበር ሙከራ (ያለ ቦታ ድምፅ ለመስጠት ሙከራ)፣ ድምፅ በሚሰጥበት ቦታ ቅስቀሳ ማድረግ፣ በተከለከለ ክልል ውስጥ የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት ናቸው፡፡

የፍትሐ ብሔር ክስ የቀረበባቸው ጉዳዮች ደግሞ ‹‹ምርጫ ይራዘም፣ የምርጫ ጣቢያዎች ይሰረዙልን፣ ዕጩ ተቀባይነት የለውም፣ አፈጻጸም፣ ፓርቲዎች ከምርጫ ይውጡልን፣ የቦርዱ ውሳኔ ውድቅ ይደረግልን፣ የመምረጥ መብት ይጠበቅ፣ በምርጫው እንወዳደር፣ የምርጫ ምዝገባ ይፈቀድልን፣ በድምፅ አሰጣጥ ሒደት ችግር የነበረባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ውጤት ይሰረዝና ምርጫ እንደገና ይካሄድ›› የሚሉ መሆናቸውን ተናግረዋል መባሉን የዘገበው ሪፖርተር ነው።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img