Sunday, September 22, 2024
spot_img

የመንግሥታቱ ድርጅት በርዳታ ሠራተኞች ላይ የደረሰው ጥቃት በገለልተኛ ወገን እዲጣራ ጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ነሐሴ 8፣ 2013 ― የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች በሠራተኞቹ ላይ የደረሰው ሞትና ጉዳት፣ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

የተባበሩት መንግሥታ ደርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ባለፉት ስድስት ወራት በትግራይ ክልል በነበረው ግጭት፣ በሌሎች አካባቢዎች ማንነታቸው ባልታወቁ የታጠቁ ኃይሎች ላይ በሚደረገው ዘመቻ፣ እንዲሁም ድንገተኛ ጥቃትና የፀጥታ ችግር ምክንያት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እየተወሳሰበ መምጣቱን አስታውቋል፡፡

በሪፖርቱ መሠረት በተገለጸው ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በደቡብና በሶማሌ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች የእርስ በርስና የጎሳ ግጭት በዕርዳታ ሠራተኞች ላይ እንግልትና ሞት ደርሷል ነው ያለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዕርዳታ ሠራተኞች ላይ በሚደረግ ገደብ ምክንያት ለዕርዳታ ፈላጊዎች ማድረስ የነበረበትን አቅርቦት ለማቅረብ፣ ከፍተኛ የሆነ መሰናክል ተፈጥሮበት እንደነበረ አስታውቋል፡፡

በስድስት ወራት ውስጥ ቢያንስ 1 ሺሕ 427 ያህል የተለያዩ ክስተቶች እንዳጋጠሙ፣ ከእነዚህ ውስጥ 127 በተመድ ሠራተኞቹ ላይ የደረሱ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ ስድስት የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች መገደላቸውን ጠቅሶ፣ መንግሥት የደረሰውን እንግልትና ጥቃት በገለልተኛ ወገን እንዲያጣራ ሲል ጠይቋል፡፡

በስድስት ወራት ውስጥ የፀጥታ ችግር፣ ውጣ ውረድ የበዛበት ተቋማዊ ማነቆና የእንቅስቃሴ ገደብ፣ የዕርዳታ ሠራተኞችን ደኅንነት በከፍተኛ ሁኔታ አደጋ ውስጥ እንደከተቱ አስታውቋል፡፡
የዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች አምቡላንስን ጨምሮ በርካታ ተሽከርካሪዎች፣ እንዲሁም የዕርዳታ መጋዘኖች መሣሪያ በታጠቁ አካላት መዘረፍና በዕርዳታ ሠራተኞች ላይ የተከፈተው የስም ማጥፋት ዘመቻ፣ በዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ መደናገጥ እንደፈጠረና ገለልተኝነታቸውን ጥያቄ ውስጥ እንዳስገባ ጠቁሟል፡፡

በአፋርና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በጎሳዎች መካከል በነበረው ግጭት፣ በአማራ ክልል ውስጥና ከክልሉ ውጪ በነበሩ ግጭቶች፣ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት የውኃ፣ የጤና፣ የትምህርትና የሌሎች መሠረተ ልማቶች አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ውስንነት እንደተፈጠረ ተመድ በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img